Thursday 2 April 2015

ሆሳዕና በአርያም

ሆሳዕና በአርያም

መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም.        በዲ/ን ሚኪያስ አስረስ

ሰውን ከወደቀበት የበደል ጉድጓድ ያወጣው ዘንድ እግዚአብሔር ክንዱን ወደ ዓለም ላከ፡፡ ሰው ሆኖ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክንድ በጉድጓድ ተጥሎ የነበረን በዚያም በሥጋ በነፍስ፤ በውስጥ በአፍአ ቆስሎ የነበረ አዳምን በትህትና በነፍስ የታመመውን በትምህርት አዳነ፡፡ ከእርሱ አስቀድሞ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከባርነት ወደ ነፃነት የሚያመጣ ባለመኖሩ እርሱ ሁሉን የፈጠረ ሁሉን የሚያኖር እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ለሰው መድኃኒት ሆነ፡፡ በሞቱም መድኃኒትነትን አሣየ፡፡ በነቢይ መድኃኒተ ፈነወ እግዚአብሔር ለሕዝቡ፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ መድኃኒትነትን ሰደደ፡፡ (መዝ.110፡9) ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፡፡

Friday 6 March 2015

መፃጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት)

የዐቢይ ጾም ስብከት (ክፍል 4)

በአያሌው ዘኢየሱስ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሰው ሁሉ በሥጋም ሆነ በነፍስ ታሞ ነበር፡፡ እርሱ ወደዚህ ዓለም የመጣው የሰው ልጆች ሁሉ አባትና መድኀኒት ስለሆነና ከዚህ በሽታቸው ሊያድናቸው ነው፡፡ ይህ ስለሆነ ወደ እኛ ከመጣ በኋላ ስለ መጣበት ዓላማ እንዲህ በማለት ተናገረን፡-   «. . . ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፤ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፤ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል. . .» ሉቃ 4፥17-19፡፡ ይህ በመሆኑም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድረ እስራኤል ተዘዋውሮ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ አድኗቸዋል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ይህን ሁኔታ የገለጸው እንዲህ በማለት ነው፡- «. . . የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር፡፡ ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ፤ አጋንንት ያደሩባቸውን፤ በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፤ ፈወሳቸውም፡፡» ማቴ 4፥23-24፡፡

Friday 27 February 2015

ምኩራብ(የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)

ምኩራብ


 የካቲት 20 ቀን 2007.ም.
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ    
እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት በዐቢይ ጾም ስምንቱ ሰንበታት ሊዘመር የተዘጋጀው የጾመ ድጓው መዝሙር ነው፡፡ በየሰንበቱ የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ፣ የሚዘመረው የዳዊት መዝሙር (ምስባክ) ከሰንበቱ ስያሜ ጋር የሚያያዙና የሚዛመዱ ናቸው፡፡ በሰንበታቱ ውስጥ የሚነበበውና የሚዘመረውም ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ያስተማራቸውን ትምህርቶችና የሠራቸውን ዋና ዋና ተዓምራትና መንክራት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ጾሙ የጌታ ጾም ስለሆነ ሁሉም መዝሙራትና ምንባባት ከጌታ ትምህርትና ሥራ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት ሦስተኛው ሰንበት ምኩራብ ተብሎ ተሰይሟል፡፡

Friday 20 February 2015

ቅድስት(የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

ቅድስት(የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

 
የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ 
ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኅበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ፡፡
 
ትርጉም:- ለእግዚአብሔር ተገዙ ስሙንም ጥሩ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው ለስሙም ምስጋናን ስጡ /አቅርቡ/ ሰንበትን አክብሩ እውነትንም አድርጉ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችኹም ተቀመጡ ክርስቶስ ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ፡፡

ምንባባት
መልዕክታት
1ኛ ተሰ.4÷1-12:- አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ÷ በእኛ ዘንድ እንደ ታዘዛችሁ በሚገባ ትሄዱ ዘንድ÷ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኙ ዘንድ÷ ደግሞ እንደ ሄዳችሁ ከፊት ይልቅ በዚሁ ታበዙና ትጨምሩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንነግራችኋለን፤ እንማልዳችኋለንም፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ያዘዝናችሁን ትእዛዝ ታውቃላችሁ፡፡

Saturday 14 February 2015

ዘወረደ

ዘወረደ

በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ
 
የዮሐ.3፥10-21  ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜ

ቁ.11. ራሱን ከዮሐንስ አግብቶ፡፡ ያየነውን፣ የሰማነውን እናስተምራለን ብዬ እንድናስተምር በእውነት እነግርሃለሁ፡፡ ምስክርነታችንን ግን አትቀበሉም፡፡

ቁ.12. ምድራዊ ልደታችሁን ስነግራችሁ ብነግራችሁ ያልተቀበላችሁኝ ሰማያዊ ልደታችሁን ብነግራችሁ እንደምን ትቀበሉኛላችሁ፡፡ ለዚህ ምክንያት አለው በጥምቀት፣ በንፍሐት ይሰጣል፡፡ ለዚያ ግን ንቃሕ ዘትነውም ባለው ነው፡፡ ምክንያት የለውምና፡፡  

ቁ.13. ወደ ሰማይ የወጣ የለም፣ ወደ ሰማይ የወጣው ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው እንጂ፡፡ ይህንስ ለምን ይሻዋል ቢሉ የወጣውም የወረደውም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው ለማለት ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ ያደረገ የለም፣ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ እውቀት ገንዘብ ያደረገ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው እንጂ፡፡

Sunday 1 February 2015

የነነዌ ሰዎች የንስሐ ምስክሮች


ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም             በዲ/ን በረከት አዝመራው
የነነዌ ጾም ከሰባቱ የቤተ ክርስቲያን አጽዋማት አንዱና የዐቢይ ጾም ማዘጋጃ ደወል ነው፡፡ ይህ የነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን በጣም ታላቅ ዋጋ ያለውና የራሱ መዝሙር የሚዘመርለት፣ ቅዳሴ የሚቀደስበት ታላቅ መታሰቢያ ያለው ታሪክ ነው፡፡
 
ራሱ ጌታችንም የነነዌ ሰዎችን የንስሐ ታሪክ በመጥቀስ አይሁድን ገስጾበታል፤ በፍርድ ቀንም በዚያ ትውልድ ዘንድ እንደሚፈርዱበት ተናግሯል፡፡ ይህም የሆነበት የነነዌ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ የንስሐ ታሪክ ስላላቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህን አስደሳች የንስሐ ታሪክ በጾመ ነነዌ ከሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባት አንጻር ለመመርመር እንሞከራለን፡፡
 
ኃጢአት ከእግዚአብሔር መለየት እንደሆነ ሁሉ ንስሐ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡  በዚህ ከእግዚአብሔር ሊለዩ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎች ባለቡት ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን ሁሉ የንስሐ ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም ጊዜ በተለየ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስባቸው የጾም ወቅቶች ሲሆኑ ከእነዚህም ታላቁና ዋነኛው ዐቢይ ጾም ነው፡፡
 

Friday 12 December 2014

በዓታ ለማርያም

በዓታ ለማርያም

በዲ/ ታደለ ፈንታው      ታኅሣሥ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.  

ይህ ዕለት የልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ መቅደስ የምትሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበትን ዕለት የምናስብበት ነው፡፡ የአምላክ እናት ከእናት ከአባቷ ቤት ተለይታ እግዚአብሔር ወደመረጠላት ሥፍራ ወደ ቤተ መቅደስ ገባች፡፡ ዕድሜዋ ሦስት ዓመት ነበር፡፡ አባታችን ኢዮብ እንደተናገረው “ሁሉን ማድረግ እንደሚቻለው፤ በባሕርይው የሚሣነው እንደሌለ አሳቡንም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል” /ኢዮ 42፡2/ አውቀን ለተጠራንበት ዓላማ መልስ መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡
 
እግዚአብሔር ሲጠራ፣ ልዑል ሲናገር የዕድሜ ጉዳይ፣ የጾታ ጉዳይ፣ የዜግነት ጉዳይ፣ የአቅም ጉዳይ፣ የጊዜ ጉዳይ፣ የስልጣን ጉዳይ፣ የእውቀት ጉዳይ፣ ሥፍራ አይገኝላቸውም፡፡ ጥያቄ ውስጥም የሚገቡ አይደሉም፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ራሳችንን ለሕይወት ዘመን አገልግሎት ልንሰጥ ይቅርና በተወሰነ ሰዓት ለሚሆነው መውጣት መግባት እየተቸገርን ነው፡፡ አገልግሎት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምንገልጽበት በሕይወታችንም ተጠቃሚ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፡-