Sunday 5 October 2014

ዘመነ ጽጌ

ዘመነ ጽጌ
«ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ ፤
ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፤ 
ድንግል ሆይ ረሐቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ››
ቅዳሴ ማርያም

ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ዘመነ ጽጌ ማለት የአበባ ዘመን ማለት ነው፡፡በሀገራችን መስከረም 25 ቀን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀምራል፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበትና ሜዳዎችንና ተራሮችን የሚያስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ የተባለ ጌታን ያስገኘች እመቤታችን በአበባ ትመሰላለችና ዘመኑ የጌታንና የእመቤታችንን ነገር በአበባና በፍሬ ለመመሰል የተመቸ ነው፡፡ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችን ስደት ታስባለች፡፡

አነ ጽጌ ገዳም … ወከመ ጽጌ ደንጐላት በማእከለ አሥዋክ ከማሁ አንቲኒ እንተ ኀቤየ በማእከለ አዋልድ

አነ ጽጌ ገዳም … ወከመ ጽጌ ደንጐላት በማእከለ አሥዋክ ከማሁ አንቲኒ እንተ ኀቤየ በማእከለ አዋልድ
መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም.
በዲ/ን በረከት አዝመራው
 
  • "እኔ የምድረ በዳ አበባ ነኝ … በሾህ መካከል ያለ የሱፍ አበባ ያማረ የተወደደ እንደሆነ አንችም በቈነጃጅት መካከል በእኔ ዘንድ እንደዚያ የተወደድሽ ነሽ፡፡" (መኃልይ. ፪፥፩)

ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ "አይንህን አንስተህ ፍጥረታትን ተመልከት፤ስለ እግዚአብሔር የሚናገሩ አሻራዎቹን በየቦታው ታገኛለህ፤ አይንህን ዝቅ አድርገህ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብብ፤ ስለ እርሱ የሚናገሩ ምሳሌዎችን ታገኛለህ" ይላል (Hymns Against Heresies)፡፡ ለኑሮ ፍጆታ ከሚጠቅመን በተጨማሪ ሥነ ፍጥረት የረቀቀውን ለመመሰል፣ ለአንክሮ ለተዘክሮ (እግዚአብሔርን በፍጥረቱ ለማመስገን) ይጠቅመናል፡፡
 
ለዐይናችን ደስታ፣ ለልቡናችን መደነቂያ ይሆኑ ዘንድ ምድርን በአበቦች ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ ሰውን ወዳጁ አምላክ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከዓመት እስከ ዓመት እግዚአብሔርን ስለመግቦቱ እና ስለ ድንቅ የእጆቹ ሥራዎች ማመስገንን አታስታጉልም፡፡ በዚህ የአበባ ወቅትም እንዲህ እያለች ትዘምራለች፦
“ነአኲተከ እግዚኦ አምላክነ
አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት
እኩት ወስቡሕ ስመ ዚአከ እግዚኦ” (ዝማሬ ዘዘመነ ጽጌ)

ትርጉሙም "ምድርን በአበቦች ውበት ያስጌጥካት አምላካችን አቤቱ እናመሰግንሃለን፤ አቤቱ ስምህ የተመሰገነ ፣የከበረ ነው" ማለት ነው፡፡ በሌላም ምስጋና፦
"ወጻእኩ ውስተ ገዳም እንዘ እሴብሖ ለእግዚአብሔር
ወበህየ ርኢኩ ኃይለ እግዚአብሔር
አዳም ግብሩ ዘኢኮነ ኃይሉ ከመ ኃይለ ሰብእ
አሠርገዎ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድርኒ አሠርገዋ በሥነ ጽጌያት
አዳም ግብሩ አዳም ግብሩ ለወልደ እግዚአብሔር"(እስመ ለዓለም ዘዘመነ ጽጌ)

ትርጉሙ "እግዚአብሔርን አመሰግን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወጥቼ በዚያ የእግዚአብሔርን ኃይል አየሁ፤ ሥራው መልካም ነው፤ ኃይሉም እንደ ሰው ኃይል አይደለም፤ ሰማይን በከዋክብት ምድርንም በአበቦች ውበት አስጌጣት፤ የእግዚአብሔር ልጅ ሥራዉ ያማረ ነው" ማለት ነው፡፡