Friday 12 December 2014

በዓታ ለማርያም

በዓታ ለማርያም

በዲ/ ታደለ ፈንታው      ታኅሣሥ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.  

ይህ ዕለት የልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ መቅደስ የምትሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበትን ዕለት የምናስብበት ነው፡፡ የአምላክ እናት ከእናት ከአባቷ ቤት ተለይታ እግዚአብሔር ወደመረጠላት ሥፍራ ወደ ቤተ መቅደስ ገባች፡፡ ዕድሜዋ ሦስት ዓመት ነበር፡፡ አባታችን ኢዮብ እንደተናገረው “ሁሉን ማድረግ እንደሚቻለው፤ በባሕርይው የሚሣነው እንደሌለ አሳቡንም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል” /ኢዮ 42፡2/ አውቀን ለተጠራንበት ዓላማ መልስ መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡
 
እግዚአብሔር ሲጠራ፣ ልዑል ሲናገር የዕድሜ ጉዳይ፣ የጾታ ጉዳይ፣ የዜግነት ጉዳይ፣ የአቅም ጉዳይ፣ የጊዜ ጉዳይ፣ የስልጣን ጉዳይ፣ የእውቀት ጉዳይ፣ ሥፍራ አይገኝላቸውም፡፡ ጥያቄ ውስጥም የሚገቡ አይደሉም፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ራሳችንን ለሕይወት ዘመን አገልግሎት ልንሰጥ ይቅርና በተወሰነ ሰዓት ለሚሆነው መውጣት መግባት እየተቸገርን ነው፡፡ አገልግሎት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምንገልጽበት በሕይወታችንም ተጠቃሚ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፡-