Friday 28 March 2014

ገብርኄር

ገብርኄር  

መጋቢት 13/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን አባተ አስፋ

 
ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርኄር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርኄር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቤተ ክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ ዐሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡