ሁሉን በጥበቡ ያደረገ እና ዓለሙ ሁሉ የእርሱ የሆነ እግዚአብሔር ፥ ሰዎች እንደአቅማቸው እና እንዲያስፈለጋቸው እንዲረዱት ባደረገው እና በሚያደርገው ሥነ ፍጥረት ሁሉ ሲታወቅ እና ሲመሰገን ይኖራል። ከዓለም እና ለዓለም ያይደሉ፣ በዓለም መሆናቸው ዓለሙን ወደተፈጠረበት ዓላማ መመለስ የሆነ ፣ ለአምላካቸው የተለዩ ክርስቲያኖችም፡- እርሱ እንዳስተማራቸው ለእግዚአብሔር ለሚያደርጉት የተለየ አገልግሎት ከራሳቸው ጀምሮ ሁሉን ይለያሉ ፤ ለዚህም ነው ቤተክርስቲያን ዘመናቱን በወንጌላውያኗ ሠይማ እና ቀድሳ፥፣ዓመቱን/፫፻፷፭ ፩/፬ቱን/ሁሉ በምድር ያለች ሰማይ ሆና መንፈሳዊ ሒደቱን በመልክ በመልኩ ለእግዚአብሔር ስትለይ ፥ መጽሐፍቱን ፣አልባሳቱን፣ ዜማውን ከነመሣሪያዎቹ፣ ..........ንዋያቱን ሁሉም እንዲሁ ለአገልግሎቷ በመለየት የሆነው።
ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምእመናን ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን በተከተለ ጥንታዊ ትውፊት፣ በተቀደሱ መንፈሳዊ በዓላት እና መንፈሳዊ መሰባሰቦች ሁሉ በጸአዳ መልበስ/ልብስ/ ማሸብረቅ ብርሃናዊነት የታወቀ፥ የተለመደ ነው። ይህም ነገር፥ የጌታን ትንሣኤ ለሴቶቹ ያበሠሩ መላእክት እንደ በረዶ ነጭ እና እጅግ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ መሆናቸውን/ማቴ ፳፰፥፫ ማር፲፮ ሉቃ፳፬፥፬ ዮሐ፳፥፲፪/ ፣ እንዲሁ ደግሞ ጌታ ሲያርግ ወደላይ አንጋጠው ሲመለከቱ የነበሩ ሐዋርያትን “....ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል” ሐዋ ፩፥፲ ያሏቸ ው መላእክት ሉቃስ እንደነገረን ነጫጭ ልብስ መልበስ ብሎም በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተለይ ደግሞ በራእይ መጽሐፍ የዚሁ ብርሃናዊ ጸአዳነት፥ ከነመልበሱ ተደጋግሞ የድል ፣የመንጻት፣ የንጽሕና እና የቅድስና መገለጫ ሆኖ መነሳትን የመሰለ፥የተከተለ ነው ። በኢትዮጵያ ምእመናን ዘንድም ይሀው ነገር፥ከዚሁ ጋር አብሮ ከየትኛውም መልበስ በላይ የሚጎነፀፈው ጸአዳ መስቀልያ መልበስ - ነጠላ ይነሳል።
በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ልዩ ሃብት ነው - ነጠላ ፤ እርግጥ ነጠላ ጋቢ፥ ጋቢን የመሰሉ ከእኛ ኃሳብ ጋርም የተስማሙ መልኮች አሉት። ምእመናን በቤታቸው ሳይቀር ጸሎት በሚያደርጉበት ጊዜ ነጭ ነጠላቸውን ለብሰው፥ “ተሰብስበን በነበረበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበር” እንዳለ ሉቃስ ሐዋ ፳፥፰ መብራትን አብርተው ነው።የሚደንቀው ደግሞ በመላ ኢትዮጵያ ማለት ይቻላል ከሰሜን እስከ ደቡብ ልብሱም ሆነ የሽመና ሙያው መኖሩ ነው።፩ ቤተክርስቲያን፥ምእመናን በመንፈሳዊ መሰባሰባቸው ፩ ሆነው አካል ሰውነታቸውን በልብስ ሰብስበው ከመያዝ በላይ ጸአዳ መልበስ ነጠላቸውንም አመሳቅለው ለብሰው ፩ ይሆናሉ።
ምእመናን ፪ትም፫ ሆነው በጸሎትም ሆነ በማኅበር ባለንበት ፣በሰንበት ት/ቤት መርሐ ግብር ፣ ይህን በመሰለውም መሰባሰብ ፥ መልእክት እንኳ ወጥቶ ለመንገር ነጠላን ካልለበስን እንዴት ይሆናል? “የተራቆትን” አይደል የሚመስለን? ምእመናን ከቦታ ቦታ ለመጓዝ ዕቃቸውን ሲሸክፉ እንኳ የማይዘነጉት ነው ይህን ለጸሎት የለዩትን ነጠላ።ይሀው በሌሎች ዘንድ እጅግ የሚያስወድደን ኢትዮጵያዊ ትውፊታችንን አይተን ለምሳሌ የአኃት አብያተክርስቲያናት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ምእመናን “የመንፈሳዊ ተሰባስቦ “አልባሳትን እንኳ ያየን እንደሁ ሴቶቹ ብቻ በተለይ በቅዳሴ ጊዜ ጸጉራቸውን የሚሸፍኑባት ሻሽ/headscarf/ ብትኖራቸው እንጂ የኛን ያህል፥እኛን መስለው ወንዱም ሴቱም “ከኖርማል” መልበሳቸው ላይ የሚያደርጉት “ምሉዕ ጸአዳ” የላቸውም።
በሃገርም ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምእመናን ግን በተገኙበት መንፈሳዊ መሰባሰብ ሁሉ በተለይ በታላቁ የአምልኮ ሥርዓት - ቅዳሴ ፣ ከውድቀት በኀፍረት በዛፍ ቅጠሎች ተከልሎ ፥ በጌታቸው እርቃን ስቅለት ድኅነታቸውን እና በትንሣኤው ብርሃን ምሥራቻቸውን ፥ የትንሣኤ ልቡና ተስፋቸውንም እየዘከሩ እና እየቀመሱ ጸአዳ ለብሰው ፣ መስቀልኛ ጸአዳ ነጠላቸውን ተጎናጽፈው በእግዚአብሔር ማዕድ ይገኛሉ።በዚሁ እንደ ምዕራባውያኑ በ”quire” ባይደለ ምእመናን ሁሉ በ፩ ድምጽ ሆነው “ይሕ”ን እየጠበቁ ተሰጥዎውን በሚመልሱበት ሰማያዊ ቅዳሴ ጸአዳቸውን ለብሰው በአምላክ ፊት ቆመው ስናያቸው እውነት እኮ እዚህ ያሉ አይመስሉም! “ ከዚህ በኋላም ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ብዙ ሰዎችን አየሁ፤ከሕዝብና፥ከአሕዛብ፥ከነገድና ከልዩ ልዩ ወገን፥ በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመዋል፤ነጭ ልብስም ለብሰዋል፥ በእጃቸውም ዘንባባ ይዘዋል።በታላቅ ቃልም ፥” በዙፋኑ ለተቀመጠው ለአምላካችን እና ለበጉ ማዳን ምስጋና ይገባል “ እያሉ ይጮሀሉ።”ራእይ ፯፥፱ ፡ አይለየን በመንግሥቱ!
ነጭነቱ እና መስቀልያ አለባበሱ በቤተክርስቲያን ያለው ምሥራቃዊ ትውፊታዊ ምሳሌያዊነት/ Eastern traditional symbolism/ ፣ በአገልግሎት ጊዜ ያለው ከባቢያዊ ምቾት እና የሚፈጥረው አንድነት፣..... ፡- ወንዱም ሆነ ሴቱ/እንደተነገረ እህቶች ጸጒራቸውንም ይሸፍኑበታል/ የሚተባበሩበትን ይህን ትውፊታዊ ፣ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያናዊ ባህላችንን እውነት ልንጠብቀው የሚገባ ሌላ ፩ነታችን ያደርገዋል - ጸአዳ መልበስ ነጠላን።
|
No comments:
Post a Comment