ከዳንኤል ክብረት
(ምንጭ- ስንክሳር- የዲያቆን መልአኩ እዘዘው ገጽ)
በእምነትታሪክ ውስጥ የታሪክ፣የአርኬዎሎጂ እናየቅርስ ጥናት ሰዎችንያስጨነቁ ሁለትጥያቄዎች አሉ፡፡ ታቦተጽዮን እና ጌታየተሰቀለበት መስቀልየት ነው ያሉት?የሚሉት ጥያቄዎች፡፡እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ አሰሳዎች፣ ቁፋሮዎች፣ መዛግብትን የማመሳከር ሥራዎች፣ አሉ የተባሉየይዞታ ጥያቄዎችን የመመርመር ፍተሻዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር ግን የዓለም ቅርሶች መናኸርያ የሆነችው ኢትዮጵያ ሁለቱንም በተመለከተ ለዓለም የምትገልጣቸው ነገሮች አሏት፡፡
ሰሞኑን በሀገራችን ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል በመከበር ላይ በመሆኑ «ለመሆኑ ጌታ የተሰቀለበት መስቀል የት ነው ያለው?» የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ያሉ መረጃዎችን እንቃኝ፡፡
በአብያተ ክርስቲያናት ከሚነገረው ትውፊት በስተቀር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎት የነበረው መስቀል እንዴት ሊጠፋ እንደቻለ የተመዘገበ ታሪክ እኔ አላገኘሁም፡፡ አብዛኞቹ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ግን አይሁድ በመስቀሉ ላይ ይደረግ የነበረውን ተአምራት በመቃወም ከክርስቲያኖች ነጥቀው እንደ ቀበሩት ይተርካሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ የቆስጠንጢኖስ የሕይወት ታሪክ /Life of Constantine/ በተሰኘው መጽሐፉ ላይ በክርስቲያኖች ዘንድ ታላቅ ሥፍራ የነበረው የጌታ መቃብር ተደፍኖ በላዩ ላይ የቬነስ ቤተ ጣዖት ተሠርቶ እንደ ነበር ይናገራል፡፡ አውሳብዮስ በዝርዝር አይግለጠው እንጂ ይህ የቬነስን ቤተ መቅደስ በጎልጎታ ላይ የመሥራቱ ጉዳይ የሮሙ ንጉሥ ሐድርያን በ135 ዓም ኢየሩሳሌምን Aelia Capitolina አድርጎ እንደ ገና ለመገንባት የነበረው ዕቅድ አካል ነው፡፡
አይሁድ በሮማውያን ላይ እስከ ዐመጹበት እና ኢየሩሳሌም ከክርስትና በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ እስከጠፋችበት እስከ 70 ዓም ድረስ መስቀሉ በክርስቲያኖች እጅ እንደ ነበር ይታመናል፡፡ በኋላ ግን ክርስቲያኖቹ የሮማውያንን እና የአይሁድን ጦርነት በመሸሽ ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ሌሎች ሀገሮች ሲሰደዱ፤በኋላም በባር ኮባ ዐመፅ ጊዜ /132-135 ዓም/ኢየሩሳሌም ፈጽማ በሮማውያን ስትደመሰስ የመስቀሉ እና የሌሎችም ክርስቲያናዊ ንዋያት እና ቅርሶች ነገር በዚያው ተረስቶ ቀረ፡፡ ንጉሥ ሐድርያንም የኢየሩሳሌም ከተማን ነባር መልክ በሚለውጥ ሁኔታ እንደገና ሠራት፡፡ ያን ጊዜ ነው እንግዲህ የቬነስ ቤተ መቅደስ በጌታችን መቃብር ላይ የተገነባው፡፡ ቆስጠንጢኖስ ለኢየሩሳሌሙ ኤጲስ ቆጶስ ለአቡነ መቃርዮስ በጻፈው እና ሶቅራጥስ እና አውሳብዮስ መዘግበው ባቆዩን ደብዳቤ ላይ ይህ ታሪክ ተገልጧል፡፡
ቀጣዮቹ 300 ዓመታት ለክርስቲያኖች የመከራ ጊዜያት ነበሩ፡፡ የሮም ቄሳሮች ክርስትናን እናክርስቲያኖችን የሚያሳድዱባቸው ዓመታት በመሆናቸው መስቀሉን የመፈለግ ጉዳይ በልቡና እንጂ በተግባር ሊታሰብ አይችልም፡፡ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱም ኢየሩሳሌም እየተዘበራረቀች እና የጥንትመልኳ እየተቀየረ በመሄዱ በጌታ መቃብር ላይም የሮማ አማልክትን ለማክበር ቤተ መቅደስ በመሠራቱ ነገሩ ሁሉ አስቸጋሪ እየሆነ ሄደ፡፡
የመስቀሉ እንደገና መገኘት
ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች መስቀሉን እንደገና ያገኘችው ንግሥት ዕሌኒመሆንዋን ይናገራሉ፡፡ በ380 ዓም አካባቢ የተወለደው ታሪክ ጸሐፊው ሶቅራጥስ Ecclesiastical History በተሰኘው መጽሐፉ ላይ በምእራፍ 17 መስቀሉ እንዴት እንደ ተገኘ ዝርዝር መረጃ ይሰጠናል፡፡ ንግሥት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ በጎልጎታ የጌታ መቃብር ላይ የተሠራውን የቬነስ ቤተመቅደስ አፈረሰችው፤ ቦታውንም በሚገባ አስጠረገችው፡፡ በዚያን ጊዜም የጌታችን እና የሁለቱ ሽፍቶች መስቀሎች ተገኙ፡፡ ከመስቀ ሎቹም ጋር ጲላጦስ የጻፈው የራስጌው መግለጫ አብሮ ተገኘ፡፡

ይህንን ታሪክ ሄርምያስ ሶዞሜን የተባለው እና በ450 ዓም አካባቢ ያረፈው ታሪክ ጸሐፊምEcclesiastical History, በተሰኘው ጥንታዊ መጽሐፉ በክፍል ሁለት ምእራፍ አንድ ላይይተርከዋል፡፡ ዞሲማን እንደሚለው በ325 ዓም የተደረገው ጉባኤ ኒቂያ ሲጠናቀቅ የቆስጠንጢኖስትኩረት ወደ ኢየሩሳሌም ዞረ፡፡
ምንም እንኳን ሶዞሜን ባይቀበለውም መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ያመለከተው ከከተማዋ በስተምሥራቅ ይኖር የነበረ አንድ አይሁዳዊ መሆኑን እና እርሱም ይህንን መረጃ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ከነበረ መዝገብ ማግኘቱን እንደ ሰማ ጽፏል፡፡ ንግሥት ዕሌኒ ባደረገችው አስቸጋሪ ቁፋሮ መጀመርያ ጌታ የተቀበረበት ዋሻ፤ ቀጥሎም ከእርሱ እልፍ ብሎ ሦስቱ መስቀሎች መገኘታቸውን ሶዞሜን ይተርካል፡፡ ከመስቀሎቹም ጋር የጲላጦስ ጽሑፍ አብሮ መገኘቱን እና የጌታ መስቀል ከሌሎች የተለየበትን ሁኔታ ከሶቅራጥስ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ይተርከዋል፡፡
ንግሥት ዕሌኒ በጎልጎታ፣ በቤተልሔም፣ በደብረ ዘይት፣ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርታ በሰማንያ ዓመቷ እንዳረፈች ሶዞሜን ይተርካል፡፡ ብዙ የታክ ጸሐፊዎች ዕረፍቷን በ328 ዓም አካባቢ መስቀሉ የተገኘ በትንም በ326 ዓም ያደርጉታል፡፡
በ457 ዓም አካባቢ ያረፈው ቴዎዶሮት የተባለው ታሪክ ጸሐፊም የመስቀሉን የመገኘት ታሪክ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ያቀርበዋል፡፡
መስቀሉ በኢየሩሳሌም
ንግሥት ዕሌኒ ለበረከት ያህል የተወሰነ ክፍል ወደ ቁስጥንጥንያ ከመውሰዷ በቀር አብዛኛውን የመስቀሉን ክፍል በብር በተሠራ መሸፈኛ አድርጋ በጎልጎታ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀመጥ ለአቡነመቃርዮስ ሰጥታቸዋለች፡፡ ይህ መስቀል በየተወሰነ ጊዜ እየወጣ ለምእመናኑ ይታይ እንደ ነበር አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በ380 ዓም ኤገርያ የተባለች ተሳላሚ መነኩሲት ቅዱስ መስቀሉ ወጥቶ በተከበረበት በዓል ላይ ተገኝታ ያየችውን ለመጣችበት ገዳም ጽፋ ነበር፡፡ /M.L. McClure and C. L. Feltoe, ed. and trans. The Pilgrimage of Etheria, Society for Promoting Christian Knowledge, London, (1919)/
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የመስቀሉ ክፍልፋዮች ወደ ተለያዩ ሀገሮች መወሰድ የጀመሩት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በሞሪታንያ ቲክስተር በተባለ ቦታ የተገኘውና በ359 ዓም አካባቢየተጻፈው መረጃ የመስቀሉ ክፍልፋዮች ቀደም ብለው ወደ ሌሎች ሀገሮች መግባት እንደ ጀመሩያሳያል፡፡ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም መስቀሉ ከተገኘ ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ በ348 ዓም በጻፈውአንድ ጽሑፍ ላይ «ዓለሙ በሙሉ በጌታችን መስቀል ክፍልፋዮች ተሞልቷል» በማለት ገልጦ ነበር፡፡ከዚህም ጋር «ዕጸ መስቀሉ እየመሰከረ ነው፡፡ እስከ ዘመናችንም ድረስ ይኼው እየታየ ነው፡፡ ከዚህ ተነሥቶም በመላው ዓለም እየተሠራጨ ነው፡፡ በእምነት ክፍልፋዮቹን እየያዙ በሚሄዱ ሰዎች አማካኝነት» ብሏል፡፡/On the Ten Points of Doctrine, Colossians II. 8./
ዮሐንስ አፈ ወርቅም የመስቀሉን ቅንጣቶች ሰዎች በወርቅ በተሠራ መስቀል ውስጥ በማድረግምእመናን በአንገታቸው ላይ ያሥሩት እንደ ነበር ጽፏል፡፡ በዛሬዋ አልጄርያ በቁፋሮ የተገኙ ሁለት ጽሑፎች የመስቀሉ ክፍልፋዮች በ4ኛው መክዘ የነበራቸውን ክብር ይናገራሉ፡፡ /Duval, Yvette, Loca sanctorum Africae, Rome 1982, p.331-337 and 351-353/፡፡ በ455ዓም በኢየሩሳሌም የነበረው ፓትርያርክ ለሮሙ ፖፕ ለልዮን የመስቀሉን ቁራጭ እንደ ላከለት ተመዝግቧል፡፡
በአውሮፓ ምድር የተዳረሰው አብዛኛው የመስቀሉ ክፍልፋይ የተገኘው ከባዛንታይን ነው፡፡በ1204 ዓም በአራተኛው የመስቀል ጦርነት ጊዜ የዘመቻው ተካፋዮች በዓረቦች ጦር ድል ሲመቱ ፊታቸውን ወደ ቁስጥንጥንያ አዙረው ከተማዋን፣ አድባራቱን እና ገዳማቱን ዘረፏቸው፡፡ በዚያ ጊዜ ተዘርፈው ከሄዱት ሀብቶች አንዱ ዕሌኒ ከኢየሩሳሌም ያመጣችው የመስቀሉ ግማድ ነበር፡፡ ይህንን ግማድ እንደ ገና በመከፋፈል አብዛኞቹ የአውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ሊዳረሱት ችለዋል፡፡ የወቅቱን ታሪክ ከመዘገቡት አንዱ ሮበርት ዲ ክላሪ «በቤተ መቅደሱ ውስጥ አያሌ ውድ ንዋያት ይገኙ ነበር፡፡ከእነዚህም መካከል ከጌታ መስቀል የተቆረጡ ሁለት ግማዶች ነበሩ፡፡ ውፍረታቸው የሰው እግርያህላል፤ ቁመታቸውም ስድስት ጫማ ይህል ነበር» ብሏል፡፡ /Robert of Clari's account of the Fourth Crusade, chapter 82: OF THE MARVELS OF CONSTANTINOPLE/
የመስቀሉ ለሁለተኛ ጊዜ መጥፋት
እስከ ስድስተኛው መክዘ ድረስ በኢየሩሳሌም ጎልጎታ የነበረው መስቀል በ614 ዓም በፋርሱንጉሥ ክሮስረስ 2ኛ /Chrosroes II/ ተወሰደ፡፡ የፋርሱ ንጉስ ኢየሩሳሌምን በወረረ መስቀሉን እናፓትርያርክ ዘካርያስን ማርኮ ወደ ፋርስ ወሰዳቸው፡፡ እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሰው ሕርቃልበ627 ዓም ባደረገው ጦርነት ክሮስረስ ድል ሲሆን ነው፡፡ ሕርቃል በመጀመርያ ወደ ቁስጥንጥንያ ካመጣው በኋላ እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በቀድሞ ቦታው በጎልጎታ አስቀምጦት ነበር፡፡
እስከ አሥረኛው መክዘ ድረስ በኢየሩሳሌም በቀድሞ ክብሩ ቢቆይም ዐረቦች አካባቢውን እየተቆጣጠሩ ሲመጡ በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ክርስቲያኖች መስቀሉን በ1009 ዓም አካባቢ ሠወሩት፡፡ ለ90 ዓመታት ያህል ያለበት ቦታ ተሠውሮ ከኖረ በኋላ በመጀመርያው የመስቀል ጦርነትጊዜ በ1099 ዓም ከተሠወረበት ወጥቶ እንደ ቀድሞው መታየት ጀመረ፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ መጥፋት
በ1187 ዓም በሐቲን ዐውደ ውጊያ ሳላሕዲን የተባለው የዓረቦች የጦር መሪ የመስቀልጦረኞችን ድል አድርጎ ኢየሩሳሌምን ሲቆጣጠር በዚያ የነበረውን መስቀል መውሰዱን አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ይገልጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን መስቀሉ የት እንዳለ እስካሁን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በወቅቱ የነበሩት የሮም ነገሥታት መስቀሉን ለማግኘት ከሳላሕዲን ጋር ብዙ ድርድር አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
በአብዛኞቹ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የመስቀሉ ክፍልፋይ እንዳለ ሁሉም ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶቹ አለ የሚባለው ክፍልፋይ ከመብዛቱ የተነሣ የሚያነሡት ትችት አለ፡፡ ጆንካልቪን «ሁሉም ክፍልፋዮች ከመስቀሉ የወጡ ከሆነ፤ እነዚህን ሁሉ ብናሰባስባቸው አንድ መርከብ የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ወንጌል ግን ይህንን መስቀል አንድ ሰው እንደ ተሸከመው ይነግረናል» ብሎ ነበር፡፡
ይህንን የካልቪንን ሂስ በተመለከተ መልስ የሰጠው ራውል ዲ ፈሌውሪ /Rohault de Fleury,/ በ1870 ዓም በዓለም ላይ አሉ በሚባሉት የመስቀል ክፍልፋዮች ላይ ጥናት አድርጎ ነበር፡፡ራውል መጀመርያ የት ምን ያህል መጠን እንዳለ ካታሎግ አዘጋጀ፤ ከዚያም መጠናቸውን አንድ ላይ ደመረ፡፡ በታሪክ እንደሚነገረው የመስቀሉ ክብደት 75 ኪሎ፣ ጠቅላላ መጠኑም 178 ኪዩቢክ ሜትርነው፡፡ ራውል ያገኛቸውና አሉ የተባሉት ክፍልፋዮች አንድ ላይ ቢደመሩ .004 ኪዩቢክ ሜትር /3.‚942‚000 ኪዩቢክ ሚሊ ሜትር/ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀሪው 174 ኪዩቢክ የሚያህለው ሜትርየመስቀሉ ክፍል ጠፍቷል ማለት ነው ብሏል፡፡ /Mémoire sur les instruments de la Passion, 1870/
ግማደ መስቀሉ በኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መዛግብት እንደሚሉት ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያየገባው በ14ኛው መክዘ በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ በግሼን አምባ የተቀመጠው ደግሞ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርጉ የነበረውን ጉዞ፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት የነበራቸውን ታዋቂነት እና ወደ ሀገረ ናግራን ተጉዘው የሠሩትን ሥራ ስንመለከት ኢትዮጵያ እስከዚያ ዘመን ድረስ b ግማደ መስቀሉን ለማግኘት ትዘገያለች ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የኢትዮጵያ ገዳም መስቀሉ ለወጣበት ቦታ እና ለጎልጎታ ያለውን ቅርበት፤ ዐፄ ካሌብም ከናግራን ዘመቻ በኋላ ዘውዳቸውን ለጎልጎታ ቤተ ክርስቲያን መላካቸውን ስናይ ይህንን የመሰለ ቅዱስ ንዋይ ኢትዮጵያውያን እስከ 13ኛው መክዘ ድረስ አንዱን ክፋይ ሳያገኙት ቆዩ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ኤርትራ ውስጥ ግማደ መስቀሉ አለበት የሚባል አንድ ገዳም መኖሩን ሰምቻለሁ፡፡
ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት ከሆነ በኋላ ነገሥታቱ በሳንቲሞቻቸው ላይ የመስቀል ምልክት ማድረጋቸው፣ እንደ ንጉሥ አርማሕ ያሉትም በበትረ መንግሥታቸው ላይ መስቀል ማድረጋቸው፤ከቀደምት ክርስቲያን ነገሥታት አንዱ የሆነው ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ተብሎ መሰየሙን ስናይ የመስቀሉ ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ቀደምት ታሪክ ያመለክተናል፡፡
በዛግዌ ሥርወ መንግሥትም ዐፄ ላሊበላ ስመ መንግሥቱ ገብረ መስቀል መባሉን፣ ሚስቱምንግሥት መስቀል ክብራ መባሏን፣ ከሠራቸው አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያ ናትአንዱ ቤተጊዮርጊስ በመስቀል ቅርጽ መሠራቱን ስናይ ኢትዮጵያውያን ከመስቀሉ ጋር ቀድመውመተዋወቃቸውን ያስገምተናል፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ መዛግብትን የማገላበጥ እና የመመርመር ሥራየሚቀረን ይመስላል፡፡
በዐፄ ዳዊት ዘመን መጥቶ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አማካኝነት በግሼን አምባ የተቀመጠው ግማደመስቀል በይፋ የታወቀውና በነገሥታቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የመጣው ዋናው እንጂ የመጀመርያውነው ለማለት ያስቸግራል፡፡
ተክለ ጻድቅ መኩርያ ግብጻዊው ጸሐፊ ማክሪዝ Historia Rerum Isi amiticarumin Abissinia በሚለው መጽሐፉ የገለጠውን መሠረት በማድረግ «የኢትዮጵያ ታሪክ ከይኩኖ አምላክእስከ ልብነ ድንግል» በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚተርኩት አስቀድሞ በሰይፈ አርእድ ዘመን በግብጹ ሡልጣን እና በኢትዮጵያዊው ንጉሥ መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር፡፡ የልዑካን ቡድኑ መሪ የኢየሩሳሌሙ ፓትርያርክ አባ ዮሐንስ ነበሩ፡፡
ልዑካኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲደርሱ ያገኟቸው ዐፄ ዳዊትን ነበር፡፡ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረውን ችግር በውይይት እና በስምምነት ፈትተው አስማሟቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ግማደ መስቀሉን እንዲልኩለት የኢየሩሳሌሙን ፓትርያርክ አቡነ ዮሐንስን አደራ አላቸው፡፡ እርሳቸውም ከግማደ መስቀሉ ጋር ሌሎች ንዋያትንም ጨምረው ላኩለት፡፡ በግብጹ ሡልጣን እና በንጉሥ ዳዊት መካከል የተፈጸመው ስምምነት ለኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች እና ነጋዴዎች ጥበቃ ማድረግን የሚያካትት ስለነበር ግማደ መስቀሉን የያዙት የዐፄ ዳዊት መልእክተኞች ያለ ችግር ኢትዮጵያ ገቡ፡፡
አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ዐፄ ዳዊት ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 1404 ዓም በድንገት ሲያርፉ ግማደ መስቀሉ በሱዳን ስናር ነበር ይላሉ፡፡ ከስናር ያነሡት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መሆናቸውንም ይተርካሉ፡፡ ተክለጻደቅ መኩርያ ግን ዐፄ ዳዊት ወደ ኢትዮጵያ አስገብተውት በተጉለት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት እንደ ነበር ይናገራሉ፡፡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የነገሡት በ1434 ዓም ነው፡፡ በእነዚህ ሠላሳዓመታትም አያሌ ነገሥታት ተፈራርቀዋል፡፡ እነዚህ ነገሥታት ግማደ መስቀሉን ለመውሰድ ያልቻሉበትን ምክንያት ማወቅ አይቻልም፡፡ ምናልባት ግን በነበረው የርስ በርስ ሽኩቻ ተጠምደው ይሆናል፡፡ ሌሎች መዛግብት እንጂ በኋላ ዘመን /ምናልባትም በዐፄ ልብነ ድንግል/ የተጻፈው የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል የግማደ መስቀሉን ነገር አይነግረንም፡፡
ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግሼን አምባ ላይ ግማደ መስቀሉን ያስቀመጠበት ሁለት ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡የመጀመርያው የአምባው የመስቀለኛ ምልክት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አምባው በዘመኑ በልዩ የንጉሠነገሥቱ ኃይል ይጠበቅ ስለ ነበር ነው፡፡ በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜም ቢሆን ሌሎች ሀብቶች ከአምባው ላይ መዘረፋቸውን እንጂ የተቀበረውን ለማውጣት ሙከራ መደረጉን የግራኝን ታሪክ የጻፈው ዐረብ ፋቂህ አያነሣም፡፡
ግማደ መስቀሉን የማውጣት ጥረት ተደረገ የሚባለው በ1851 ዓም ዐፄ ቴዎድሮስ በጣም የሚወዷቸው ባለቤታቸው እቴጌ ምንትዋብ ከሞቱ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው፡፡ ንጉሥ ቴዎድሮስ እቴጌ ምንትዋብን እጅግ ይወዷቸው ስለነበር በመስቀሉ አማካኝነት ከሞት ለማስነሣት አስበው ነበር፡፡ይህንንም በወታደሮች ኃይል በማስቆፈር አስጀምረውት ነበር፡፡ በመካከል ግን ከጉድጓዱ ኃይለኛ ሽታ እና ጢስ ወጥቶ ከቆፋሪዎቹ የተወሰኑትን በመግደሉ ሃሳባቸውን ሠርዘው ባለቤታቸውን በግሼን አምባ ቀብረው ተመልሰዋል፡፡
መስቀሉ እንዴት ጠፋ?

አይሁድ መስቀሉን፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን እና የጌታችንን መቃብር የተቆጣጠሩት እናክርስቲያኖች እንዳይገቡ ያገዱት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ጎልጎታ የከተማዋ ጥራጊ እንዲደፋበትአዘዙ፡፡ ምክንያቱም በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢዋ አብያተ ክርስቲያናት አልነበሩም፡፡ክርስቲያኖች ግን በጌታችን መቃብር አካባቢ ዋሻዎችን ፈልፍለው ይገለገሉባቸው ነበር፡፡
ዛሬ በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም ክልል የሚገኘው ጎልጎታ በዚያ ዘመን ከከተማዋ ውጭ ነበር፡፡ጌታንም የሰቀሉት ከከተማ አውጥተው ነው፡፡ አይሁድ የከተማ ጥራጊ መድፊያ እንዲሆን የፈለጉትምቦታው ከከተማ የወጣ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር ነው፡፡
ይህ ታሪክ በስንክሳራችን ከተጻፈው ታሪክ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡
መስቀሉ የት ተቀበረ?
አንዳንድ አካላት የሚተርኩት ታሪክ በስንክሳራችንም ሆነ በጥንታውያን መዛግብት ከተገለጠውየተለየ ነው፡፡ በመስከረም 17 እና በመጋቢት 10 የሚነበበው ስንክሳራችን መስቀሉ የተቀበረው በዚያው በጎልጎታ እንደሆነ ይተርካል፡፡ «የጎልጎታን ኮረብታ ባስጠረገች ጊዜ የከበረ መስቀልን አገኘችው» ይላል፡፡ አንዳንድ አካላት ግን መስቀሉን አይሁድ በሌላ ቦታ ጉድጓድ ቆፍረው እንደቀበሩት ይገልጣሉ፡፡
በስንክሳራችን የተገለጠው እና መስቀሉ የተቀበረው በጎልጎታ ነው የሚለው ታሪክ በሦስተኛው እና በ4ኛው መክዘ ከነበሩት የታሪክ ጸሐፊዎች ገለጻ ጋር አንድ ነው፡፡ በ380 ዓም አካባቢ የተወለደው ታሪክ ጸሐፊው ሶዜማን መስቀሉ የተገኘው ከጎልጎታ መሆኑን መዝግቦ አቆይቶናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ መስቀሉ በጎልጎታ ተቀብሮ ነበር የሚለው የስንክሳራችን ትረካ ከግብጽ፣ከሶርያ እና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ስንክሳር ትረካ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡
በሦስተኛ ደረጃም እሌኒ ንግሥት መስቀሉን ቆፍራ ያወጣችበት እና በኋላም የመስቀሉን ቤተክርስቲያን የሠራችበት ቦታ የሚገኘው በዚያው በጎልጎታ፣ ያውም ከኢትዮጵያ የዴር ሡልጣን ገዳም ሥር ነው፡፡
በመሆኑም መስቀሉን አይሁድ በሌላ ቦታ ቀበሩት የሚለው ሃሳብ የሚያስኬድ አይመስልም፡፡
መስቀሉ እንዴት ተገኘ?
መስቀሉ እንዴት እንደ ተገኘ በቤተ ክርስቲያናችን የሚገለጠው ታሪክ ከሌሎች ጥንታውያንመዛግብት ታሪክ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ መስቀሉን ያወጣችው የቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ መሆንዋን ሁሉም ይስማሙበታል፡፡
እሌኒ ንግሥት ወደ ኢየሩሳሌም ስትገባ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡ለዚህም ሦስት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የመጀመርያው በኢየሩሳሌም ከ132 እስከ 135 በተደረገው እናከተማዋ ፈጽማ በጠፋችበት ጦርነት ምክንያት ክርስቲያኖች ከከተማዋ ርቀው መኖራቸው ነው፡፡ሁለተኛው ደግሞ አይሁድ መስቀሉን በጎልጎታ ከቀበሩ በኋላ መጀመርያ ጥራጊ መድፋታቸው ሲሆንሦስተኛው ንጉሥ ሐድርያን በ135 ዓም የኢየሩሳሌምን ገጽታ የቀየረውን አዲስ ፕላን በማውጣት ከተማዋን እንደገና መሥራቱ፤ በጎልጎታም ላይ የቬነስን መቅደስ መገንባቱ ነው፡፡ የቬነስ መቅደስ መገንባት ክርስቲያኖች ወደ አካባቢው ፍጹም እንዳይቀርቡ አስከላከላቸው፡፡
ንግሥት እሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ገብታ ያደረገችውን ስንክሳራቸውን እንዲህ ይተርከዋል «እርሷ በመጣች ጊዜ የጌታችን የክርስቶስን መቃብር እስካሳዩዋት ድረስ አይሁድን ይዛ አሰቃየቻቸው፤ ያንን ኮረብታም እስከ ጠረጉ ድረስ አስገደደቻቸው፤ የከበረ መስቀሉም ከተቀበረበት ተገልጦ ወጣ» ይላል፡፡በሌላም በኩል የመጋቢት 10 ቀኑ ስንክሳር ታሪኩን ያውቃል የተባለውን አንድን አይሁዳዊ አሥራ በማስጨነቅ ምሥጢሩን እንዳውጣጣችው ይገልጣል፡፡ ይህ አገላለጥ ከጥንታውያን መዛግብት አገላለጥ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ዞሴማን አልተቀበልኩትም ቢልም አንድ አይሁዳዊ ሽማግሌ ለንግሥት እሌኒ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ እንዳሳያት የሚተርከው ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን ኪርያኮስ የተባለ አረጋዊ ነገራት እየተባለ ከሚተረከው ጋር ተመሳይ ነው፡፡ በወቅቱ ይህ አይሁዳዊ ስለ ዕጣንም ሆነ ጸሎት ሊናገር የሚችል አይመስልም፡፡ ይህ ሃሳብ ምናልባት በወቅቱ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የአቡነ መቃርዮስ ይሆናል፡፡
እስካሁን እኔ በሌሎች መዛግብትም ሆነ በስንክሳራችን ላይ ያላገኘሁት «ደመራ ተደምሮ ጢሱ አመለከተ» የሚለውን ታሪክ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ጢሱ ለመስቀሉ መስገዱን ይገልጣል፡፡ እሌኒ ንግሥት ክርስቲያናዊት እናት እንደ መሆንዋ መጠን አይሁድ የሰጧትን መረጃ ብቻ ተቀብላ ቁፋሮ አታስጀምርም፡፡ በአይሁድ የተነገረው በጸሎት እንዲረጋገጥ አድርጋለች፡፡ ያን ጊዜ ጸሎት ተደርጎ ዕጣን ሲታጠን ጢሱ ወደ ጎልጎታ አመለከተ፡፡ ይህንን በተመለከተ መዛግብትን ማገላበጥ ይቀረናል፡፡
በዓለ መስቀል እንዴት ተወሰነ?
በኢትዮጵያም ሆነ በግብጽ ያሉ ስንክሳሮች ላይ መስቀሉ የተገኘው መስከረም 17 ቀን መሆኑንይገልጣሉ፡፡ ቁፋሮው መቼ እንደተጀመረ በትግጠኛነት የሚገልጥ መረጃ አላገኘሁም፡፡ የኛ ሊቃውንት ቁፋሮው መስከረም 17 ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን መጠናቀቁን ይገልጣሉ፡፡ በወቅቱ ከነበረው ቴክኖሎጂ አንፃር ሊወስድ ይችላል፡፡ መጋቢት 10 ቀን ግን ራሱን የቻለ ታሪክ አለው፡፡ መስቀሉ በፋርሶች ከተማረከበት በንጉሥ ሕርቃል ተመልሶ ወደ ጎልጎታ የገበባበት ቀን ነው፡፡
የቀድሞ አባቶች ታክን ከታሪክ ማገናኘት ልማዳቸው ነውና መስቀሉ መጋቢት 10 ቀን ወደጎልጎታ እንዲገባ ያደረጉት ቀድሞ ከተገኘባት ቀን ጋር ለማስተሣሠር ሊሆን ይችላል፡፡ በስንክሳራችንመስከረም 16 ቀን በኢየሩሳሌም እና በአካባቢው በንግሥት እሌኒ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት በመስቀሉ የተባረኩበት ቀን መሆኑን ይነግረናል፡፡ መስከረም 17 ቀን ደግሞ ቅድስት እሌኒ መስቀሉ በተገኘበት በጎልጎታ ያሠራችው የመስቀሉ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ነው፡፡
ነገር ግን በዐቢይ ጾም በዓል ስለማይከበር የመስቀሉ በዓል ቅዳሴ ቤቱ በተከበረበት ቀን በመስከረም 17 እንዲከበር ሊቃውንት ሥርዓት መሥራታቸውን ስንክሳሩ ይነግረናል፡፡
እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ገባ?
ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደገባ ሁለት ዓይነት ታሪኮች አሉ፡፡ አንዱ ከግብጽ ሁለተኛው ከኢየሩሳሌም፡፡ ለመስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ምክንያት የሆነው በዐፄ ሠይፈ አርእድተፈጥሮ የነበረ ችግር ነው፡፡ በዚህ ዘመን የግብጽ ሡልጣኖች በግብር እያመካኙ የግብጽ ክርስቲያኖችን ባሰቃዩዋቸው ጊዜ ንጉሥ ሠይፈ አርእድ እስከ ደቡብ ግብጽ እየዘመተ ወግቷቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ የንግድ መሥመሩን ከለከለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ እና ከኑቢያ የሚሄደው ዕቃ ተቋረጠ፡፡
ሁኔታው ከሥጋት ላይ የጣላቸው የግብጽ ሡልጣኖች በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ የጣሉትን ቀንበር አላሉ፡፡ የግብጹ ጳጳስ እና ሡልጣኑ ተስማምተው ወደ ኢትዮጵያ መልክተኛ ላኩ፡፡ በጉዳዩም በኢየሩሳሌም የነበሩት ፓትርያርክ ዮሐንስ ገቡበት፡፡ አቡነ ዮሐንስ የመልክተኞቹ መሪ ሆነው መጡ፡፡
በጊዜው በዙፋኑ ላይ የነበረው ዐፄ ዳዊት ስለነበረ እርሱም ንግዱን ላይዘጋ ሡልጣናቱም ክርስቲያኖቹን ላያጉላሉ ተስማሙ፡፡ ለስምምነቱ ማሠርያ ይሆን ዘንድም ከጌታ ግማደ መስቀል እንዲመጣለት ንጉሥ ዳዊት ጠየቀ፡፡ ሡልጣኑም ተስማማ፡፡
በ1387 ዓም ግማደ መስቀሉን የሚያመጡ ሊቃውንት ወደ ካይሮ ተላኩ፡፡ መልክተኞቹ ለሡልጣኑ የሚሰጥ በ20 ግመል የተጫነ ስጦታ ይዘው ነበር፡፡ ዐፄ ዳዊት አስቀድሞ ሃሳቡን ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ለአቡነ ዮሐንስ ነግሯቸው ስለነበር እርሳቸው ሉቃስ የሳላትን ሥዕል፣ ኩርአተርእሱ የተባለውን የጌታ ሥዕል እና ግማደ መስቀሉን ላኩለት፡፡ ግማደ መስቀሉ መስከረም 16 ቀንተጉለት ገብቶ ንጉሡ ባሳነፁት ቤተ ክርስቲያን የቀመጠ፡፡ /ተክለ ጻድቅ መኩርያ፣ ከይኩኖ አምላክእስከ ልብነ ድንግል፣ ገጽ 116-118/
በሌላ በኩል ደግሞ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ለመቀበል ዐፄ ዳዊት ወደ ስናር ወርደው ነበር፡፡ በዚያም ባዝራ ፈረስ ጥላ ስለረገጠቻቸው ሞቱ፡፡ ግማደ መስቀሉም በስናር ቆየ የሚል ታሪክም አለ፡፡ ይህንን ታሪክ ለመቀበል የሚከብደው በወቅቱ ሱዳን በዐረቦች መወረሯን፤ስናርም ለግዛታቸው ቅርብ የነበረ መሆኑን ስናስበው ነው፡፡ ከዚህም በላይ ከዐፄ ዳዊት እስከ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ሠላሳ ዓመታት በዚያ ተቀመጣ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምናልባትም የተክለ ጻድቅ መኩርያ ትረካ የተሻለ ይመስለኛል፡፡
በሌላም በኩል ግማደ መስቀሉ ከኢየሩሳሌም መጣ የሚለው ታሪክ በወቅቱ ኢየሩሳሌም ከነበረችበት ሁኔታ አንፃር ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በ1187 ዓም ሳላሕ ዲን ኢየሩሳሌምን ከያዛት በኋላ መስቀሉ ከአካባቢው ተሠውሯል፡፡ የሮም ነገሥታትም እርሱን ለማግኘት ተደራድረው አልተሳካላቸውም፡፡ የመስቀል ጦረኞችም ቢሆኑ ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ሌሎችን ንዋያት አመጡ እንጂ መስቀሉን አላገኙትም፡፡
እንደ እኔ ግምት ግማደ መስቀሉን ያገኘነው ከእስክንድርያ መሆን አለበት፡፡ ንግሥት እሌኒ የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናትን ሠርታ ስታጠናቅቅ የቁስጥንጥንያ፣ የአንፆኪያ እና የእስክንድርያ አባቶች ካህናትን ልከዋል፡፡ ግማደ መስቀሉ ወደ እስክንድርያ የገባው በዚያ ዘመን ሳይሆን አይቀርም፡፡በኋላም ዐፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ሲጠይቅ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ላደረገው ውለታ ልከውለት ይሆናል፡፡ በሌላም መልኩ ሡልጣኑም ግፊት ማድረጉ አይቀርም፡፡
አያሌው ተሰማ የተባሉ ምሁር «ታሪክ ነው ገበያ፣ የሁሉ መዋያ» በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ዐፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ያገኘው ዓባይን ገድቦ ግብፆችን በማስጨነቅ ነው ይላሉ፡፡ ሁኔታው ያሰጋቸውየግብጽ ባለ ሥልጣናት ለላኳቸው መልክተኞች ግማደ መስቀሉን እንዲሰጧቸው በመጠየቃቸውሡልጣናቱ ግብፃውያኑን አባቶች ተጭነው እንዳሰጧቸው ይተርካሉ፡፡
ደመራ
የደመራ በዓል መላዋን ኢትዮጵያ ከሚያስተሣሥሩት በዓላት አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንትየደመራ በዓል መነሻ ንግሥት እሌኒ ናት ይላሉ፡፡ ነገር ግን ስለ ንግሥት እሌኒ በተጻፉት ጥንታውያንመዛግብት ሁሉ ይህንን የሚደግፍ ነገር አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናት ቅዳሴቤት ሲከበር አበው ሊቃነ ጳጳሳት መስቀሉን ይዘው ችቦ አብርተው እየዞሩ መባረካቸውን የሚገልጡመዛግብት አሉ፡፡
ኢትዮጵያውያንም ይህንን በመያዝ የመስቀልን በዓል በደመራ በዓል ማክበር ጀምረዋል፡፡ ደመራየአባቶቻችን የመንፈሳዊ ብቃት መገለጫ እንጂ ከውጭ አልመጣም፡፡ የጌታችንን ጥምቀት በዓል ታቦቱንበበዓለ ከተራ ይዞ በመውረድ እና በበዓሉ እንዲመለስ ሥርዓት እንደሠሩት ማለት ነው፡፡
የደመራ ሥርዓት ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ በተመሳሳይ ሰሞን እና ሥርዓት ይከበራል፡፡የደቡብ ኢትዮጵያ ወርቃማው የክርስትና ዘመን የሚባለው ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን እስከ ዐፄዘርዐ ያዕቆብ ያለው ዘመን ነው፡፡ የመስቀል ደመራ ሥርዓት በደቡብ ውስጥ የሠረፀው እና መከበርየጀመረው በዚህ ዘመን ወይንም ቀደም ብሎ መሆን አለበት፡፡ አንድን ሥርዓት ባህል ለማድረግ ብዙመቶ ዓመታት ያስፈልጋልና፡፡
በደቡብ ግራኝ ሊያጠፋቸው ካልቻሉ ክርስቲያናዊ ሥርዓቶች አንዱ መስቀል ነው፡፡ በወላይታ፣በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጉራጌ፣ በከፋ ሸካ ከነ ክብሩ እና ሞገሡ አሁንም ይከበራል፡፡ አንዳንድ ሕዝቦች ትምህሩጠፍቶባቸው እንኳን ሥርዓቱን አልረሱትም፡፡
ይህ ነገር የደመራ በዓል ከግማደ መስቀሉ መምጣት በፊት በሀገራችን ሊኖር እንደሚችልያመለክታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዜና መዋዕሎችን እና መዛግብትን ማገላበጥ ገና ይቀረናል፡፡
በሌላም በኩል የደብረ ታቦርን እና የአዲስ ዓመት መለወጫን በዓል በደመራ እና በችቦየማክበሩ ባህላችን ደመራ ከመስቀል በዓል ጋር ብቻ የተያያዘ አለመሆኑን ፍንጭ ይሰጠናል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይህንን ችቦ የማብራት ሥርዓት ከጥንት ሀገራዊ ባህል እናከኢየሩሳሌም መብራት የማውጣት ሥርዓት የቀመሩት ይመስላል፡፡ በኢየሩሳሌም ከጌታ መቃብርበየዓመቱ ለበዓለ ትንሣኤ መብራት የማውጣት ሠርዓት ነበር፡፡ ይህ ሥርዓት ልዩ ልዩ የፈትል እና ዘይትመብራቶችን በአንድነት አስተሣሥሮ ይዞ መውጣት ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት በኢትዮጵያዊው ችቦበመወከል በበዓል ቀን እንዲበራ ሥርዓት የሠሩልን አባቶች በረከታቸው ይደርብን፡፡
No comments:
Post a Comment