የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ ቅርስነት ተመዘገበ |
ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኢትዮጵያ የመሰቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች (Intangible) በቅርስነት መመዝገቡን አስመልከቶ ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡ አቶ ዮናስ ደስታ የፌደራል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክተር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ (Intangible) ሆኖ የተመዘገበው ዩኔስኮ የሚጠይቀውን ሒደት ጠብቆና የተለያዩ የግምገማ መሥፈርቶችን አልፎ አዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ከኅዳር 23 – 28 ቀን 2006 ዓ.ም. እያደረገ ባለው ስምንተኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ላይ በትናንትናው ዕለት ተቀብሎ አጽድቆታል” በማለት ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮናስ የመስቀል በዓል አከባበርን በቅርስነት ለማስመዝገብ የተደረገውን ጥረት ሲገልጹ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያዎች አማካይነት ጥናቱ ተከናውኖ ሰነዱ ለዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ኖሚኔሽን በ2004 ዓ.ም. መቅረቡን አውስተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘገቡ ለጉባኤው ከቀረቡት 31 የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል 23ቱ ሲመረጡ የመስቀል በዓል አከባበር ከተመረጡት ውስጥ አንዱ በመሆኑና እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ የሰሜን ተራሮች፤ አክሱም ጸዮን ሐውልቶች፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፤ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፤ ጢያ ትክል ደንጋዮች፤ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፤ ሐረር ጀጎል፤ የኮንሶ ባሕላዊ መልክአ ምድር እና የፋሲል ግቢ ኢትዮያ ከዚህ ቀደም ያስመዘገበቻቸው የሚዳሰሱ (tangible) ቅርሶች መካከል ዘጠኙ ሲሆኑ ብቸኛው የመስቀል በዓል አከባበር ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ይመደባል፡፡ ምንጭ |
No comments:
Post a Comment