Wednesday 8 August 2012

ጾመ ፍልሰታ


ነሐሴ 1 ቀን 2004 ዓ.ም.
በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡ ፈጣሪያችን ጾሙን የበረከት፣ የረድኤት የንስሓ ያደርግልን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ ንስሓ ገብተን፣ ጾመን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን ሕይወት እንድናገኝ የፈጣሪያችን ቸርነቱ አይለየን! አሜን

ጾም፡- መተውን መከልከልን መታቀብን፣ መታረምን የሚገልጥ የግብር ስም ነው፡፡

kidaseየቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓትና የሕግ መጽሐፍ የሆነው ፍትሐ ነገሥት በ15ኛው አንቀጹ መግቢያ ላይ “ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው፡፡ በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕጉን ለሠራለት እየተታዘዘ የፈቲዉን ኀይል ያደክምበት ዘንድ ለነባቢትም ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ፤” በማለት የጾምን ምንነትና ጥቅም አጠር አድርጎ ያብራራል፡፡

ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው፡፡ ለሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ የሚጾም ሰው በጾም ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን እንደሚጠቅም ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ነው፡- “ከኀጢአት ፆር ከፍትወት አንዱንም ድል ለመንሣት ለማጥፋት በጾም መድከም የሥራ ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነች የታወቀ ነው፡፡ የሥራ ሁሉ መጀመሪያ በጾም መድከም ነው፡፡ ይልቁንም በባሕርያችን የምትኖር ኀጢአትን ለሚዋጋ ሰው” በማለት ማር ይስሐቅ የተባለው መጽሐፋችን የሚናገረው፡፡ በማር ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6 ላይ ጾምን በተመለከተ የሰፈረው መግለጫ “ጾም፡- የሥራ መጀመሪያ ናት፤ የጽሙዳን ክብራቸው ናት የድንግልና የንጽሕና ጌጻቸው ናት፤ የንጽሕና መገለጫ ናት፡፡ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ ናት፡፡ የጸሎት ምክንያት ናት፡፡  የዕንባ መገኛ ናት፡፡ አርምሞን የምታስተምር ናት፡፡ ለበጎ ሥራ ሁሉ ታነቃቃለች” የሚለው ይገኝበታል፡፡

ከዚህ በላይ እንደተመለከተው ጾማችንን ከጸሎት ከምጽዋት ከሰጊድ እንዲሁም የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ጭምር ልናስተሳስረው ይገባናል፡፡ አለዚያ ጾማችን ከእህልና ከውኃ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ የምንከለከልበት ከሆነ እንደ ድልድይ ሆኖ ከፈጣሪያችን አያገናኘንም ግዳጅም አይፈጽምልንም፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- “ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውን ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ፡፡ ስለምን ጾምን ፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ፡፡

እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ፡፡ እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤… እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንዲህ ባለቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፋትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፥ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሸግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንስ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል፡፡ የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል ትጮኻለህ እርሱም እንሆኝ ይላል፡፡” /ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ.58፥2-9

ብሉይን ከሐዲስ አስማምታ የምትቀበል ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የጾምንና የጸሎትን ሥርዓት ሠርታ እኛን ልጆቿን ለበረከት፣ ለሕይወት ለዘላለማዊ፣ ክብር ለማብቃት ታስተምረናለች፣ በሥርዓቷም ትመራናለች፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የጾም ዓይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም የግል /የስውር/ እና የዐዋጅ አጽዋማት ይባላሉ፡፡

I.    የግል /የስውር/ ጾም
ምእመናን በልዩ ልዩ ምክንያት ከመምህረ ንስሓቸው ጋር በመመካከር በፍቃድ የሚጾሙት የጾም ዓይነት ነው፡፡ ይህም በሌላ አካል የማይታወቅና ሊታወቅ የማይገባ ነው፡፡ በንስሓ ምክንያት ከሚጾመው በተጨማሪ ስለቤተሰብ ስለወገን፣ ስለ ሀገር…. ወዘተ ተብሎ የሚጾሙት ጾም ይኖራል፡፡ ይህ ከዐዋጅ ጾም ከሚለይባቸው ምክንያቶች አንዱ በምሥጢር የሚጾም በመሆኑ ነው፡፡ በንስሐ ምክንያት ወይም በሌላ /በራሱ ፈቃድ የሚጾም ሰው መጾሙን ካሳወቀ እንደ ግብዝነት ከንቱ ውዳሴ ይሆንበታል፡፡ ይህ መሆኑም ዋጋ አያሰጠውም፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል፡፡” በማለት አስበ ጸሎታችንን /የጸሎታችንን ዋጋ/ ከፈጣሪ እንድናገኝ “እዩኝታን” /እዩልኝ፣ እወቁልኝ/ ከሚል የግብዝነት ሕይወት ተላቀን ልንጾመው እንደሚገባ አዞናል፡፡ /ማቴ.6፥16-18/

II.    የማኅበር /የዐዋጅ/ ጾም
በዐዋጅ ለሕዝቡ ተነግሮ ሕዝቡ ሁሉ ዐውቆት በአንድነት የሚጾም ጾም ነው፡፡ ሁሉም በአንድነት ወጥ በሆነ መልኩ የሚጾመው በመሆኑ ከንቱ ውዳሴ የለውም፡፡ ፈሪሳዊም አያሰኝም፡፡ በዐዋጅ ጾም አንድ ሰው እጾማለሁ ቢል በውስጡ እስካልታበየና እስካልተመካ ድረስ ጾምን ሰበከ ይባላል እንጂ ውዳሴ ከንቱ አምጥቶበት ዋጋ አያሳጣውም፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ምእመናን ሁሉ እንድንጾማቸውና በሥጋም በነፍስም እንድንጠቀምባቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የዐዋጅ አጽዋማት አሉ፡፡ እነዚህም በቅዱሳን አባቶቻችን በሐዋርያት ሲጾሙ የቆዩና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቀኖና ያጸኗቸው ዲድስቅሊያና ሌሎች የቀኖና መጻሕፍት ሥርዓታቸውን የሠሩላቸው ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓመት ውስጥ የሚጾሙት ሰባቱ አጽዋማት በጊዜ ቀደም ተከተላቸው መሠረት፡-

  1. ጾመ ነቢያት /ከኅዳር 15-ታኅሣሥ 29/
  2. ጾመ ነነዌ /ከጾመ ሁዳዴ መግቢያ 15 ቀን በፊት ያሉት ሦስት ቀናት ከሰኞ እስከ ረቡዕ/
  3. ጾመ ሁዳዴ /ከጾመ ነነዌ 15 ቀናት በኋላ፤ ለ55 ቀናት ይጾማል/
  4. ጾመ ገሃድ /የገና ዋዜማ እና ጥር 10 ቀን/
  5. ጾመ ድኅነት /ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ከሚመጣው ረቡዕ ጀምሮ/
  6. ጾመ ሐዋርያት ከበዓለ ሃምሳ ማግስት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 5/
  7. ጾመ ፍልሰታ /ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 14 ቀን፡፡

ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት አጽዋማት ለአሁኑ ጾመ ፍልሰታን እንመለከታለን
“ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፥8/

“ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎተ ኰኲሕ ቅሩበ ጥቅም፡፡ አቅራቢያዬ መልካሟ ርግብየ ተነሽ፤ ነዪ፤ በግንቡ አጠገብ ወዳለው ወደ ዋሻው ጥላ፡፡” /መኃ.2፥10-14/

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን መቅደሱ፥ ታቦቱ፣ ማደሪያው፣ መንበሩ እናቱ አድርጎ መረጣት፡፡ ስለዚህ ምክንያት አብ ጠበቃት ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ከርሷ ተዋሐደ መንፈስ ቅዱስ አጸናት፡፡ እመቤታችን በዚህ ኃላፊ ዓለም ለ64 ዓመት ቆይታለች፡፡ ጥር ሰኞ ይብታል ሰኞ እስከ ሰኞ 8 ሰኞ እስከ ሰኞ 15፣ ሰኞ እስከ ሰኞ 22፣ ሰኞን ትቶ እሑድ ጥር 21 ቀን እመቤታችን አርፋለች፡፡ ሐዋርያት ባጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ “ቀድሞ ልጇን ሰቅለን ብንገድለው ደቀ መዛሙርቱ ተነሣ፣ ዐረገ” እያሉ ሲያውኩን ኖሩ፤ ዛሬ ደግሞ እርሷን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን” ብለው ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል የታውፋንያን ሁለት እጁን በሰይፍ መትቶ ቀጣው፡፡ በዚህም የታውፋንያ ሁለት እጁ ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡ ከዚያ በኋላ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌላዊውን ቅዱስ ዮሐንስ ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፡፡

ሐዋርያት ዮሐንስን “እንደምን ሆነች” አሉት፡፡ እርሱም፡- “በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች” አላቸው፡፡ “ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው፤ በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፤ ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን ጀምረው እሑድ ነሐሴ 14 ቀን ፈጽመዋል፡፡ በዚሁ ቀን ጌታችን ትኩስ በድን አድርጎ የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ እርሷም እንደ ልጇ በተቀበረች በሦስተኛው ቀን /ማክሰኞ/ ተነሥታ አርጋለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ” ያሰኘውም ይህ ነው፡፡ በዚሁ ጊዜ ከሐዋርያት ወገን የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ /ከሕንድ/ ሲመጣ ስታርግ አገኛት፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ይላል፤ ተበሳጨ፡፡ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁኝ” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የልቡናን ሐዘን የምታቀል እመቤታችን፡- አይዞህ አትዘን እኒያ ትንሣኤዬን ዕርገቴን አላዩም፡፡ አንተ አይተሃል፡፡ ተነሣች፣ ዐረገች ብለህ ንገራቸው፡፡” ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚህ በኋላ ሄዶ፤ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው “ሥጋዋን አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ እንጂ ልማድህ ነው፡፡ አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም፤ አንተ እየተጠራጠርህ ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራለህ” አለው፡፡ እርሱም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ይሰማቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ተቆጥቶ ሂዶ መቃብሩን ቢከፍተው የእመቤታችን ሥጋዋን አጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ደንግጦ ቆመ፡፡ ይህን ጊዜ ቅዱስ ቶማስ “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች” አላቸው፡፡ የያዘውንም ሰበን እያሳያቸው፡- “ቅዱስ ሥጋዋን የገነዛችሁበት ጨርቅ /ሰበን/ ይህ አይደለምን” ብሎ ሰበኑን ሰጣቸው፡፡ ይህንንም ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ከዚህ በኋላ በዓመቱ “ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ በማለት ጾም ጀመሩ፡፡ በ16ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ ቄስ፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ራሱ ቀድሶ አቁርቦአቸዋል፡፡

ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጌታችን በኋላ ከክርስቲያኖች ሁሉ በፊት የትንሣኤንና የዕርገትን ክብር አግኝታ ልዑል እግዚአብሔር ባዘጋጀላት ልዩ ሕይወት እንደምትኖር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

ምእመናን ሁላቸውም በየጾታቸውና በየመአረጋቸው ቀን በቅዳሴ፣ ሌሊት በሰዓታት በማኅሌት በኪዳን ቃለ እግዚአብሔርን በመስማትና ስብሐተ እግዚአብሔርን በማድረስ ይወሰናሉ፡፡

በእነዚህ አሥራ አምስት ቀናት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ውዳሴዋና ቅዳሴዋ ተራ በተራ ይተረጎማሉ፡፡ ምእመናንም በፍቅርና በሃይማኖት የሚሰጠውን ትምህርት ይሰማሉ፡፡

ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ባመሰገነበት በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ከተናገራቸው ኀይለ ቃላት፡- “ነጸረ አብ እምሰማይ፡፡ ወኢረከበ ዘከማኪ፡፡ ፈነወ ዋሕዶ ወተሰብአ እምኔኪ፡፡ ማለትም እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ አየ፤ አየና እንዳች ያለ ባያገኝ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን ልጁን ወዳንቺ ላከው፡፡ ካንቺም ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ሆነ፡፡” በማለት ያመሰገነበት ቃል ይገኛል፡፡ /ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ/ ይህ ቃል እመቤታችን ከፍጥረታት ሁሉ የከበረች በንጽሕናዋና በቅድስናዋ የተነሣ አምላክ ከእርሷ ተወልዶ /ሰው ሆኖ/ ዓለምን እንዲያድን ምክንያት የሆነችበትን ያስረዳል፡፡ በዳዊት መዝሙር ሰፍሮ በምናገኘው ቃል እግዚአብሔር አምላካችን የሚያስተውል እርሱንም የሚፈልግ ልብ ከሰዎች ልጆች እንዲያገኝ ቢመለከት አንዳች እንኳ እንዳጣና ሁሉ እንዳመፁ ተጠቅሶአል፡፡ /መዝ.13፥2-3/ ስለሆነም ነው ይህንኑ ቃል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው፡- “በአማን ነጸረ እግዚአብሔር አብ እምሰማይ ምሥራቀ ወምዕራበ ሰሜነ ወደቡበ፡፡ አስተንፈሰ ወአጼነወ፡፡ ወኢረከበ ዘከማኪ፡፡ ወሠምረ መዓዛ ዚአኪ፡፡ ማለትም እግዚአብሔር በልዕልና ሆኖ አራቱን ማዕዘን በእውነት ተመለከተ አስተናፈሰ አሸተተ ነገር ግን በንጽሕና በቅድስና የተዘጋጀች እንዳንቺ ያለች አላገኘም፡፡ መዓዛ ንጽሕናሽን መዓዛ ቅድስናሽን ወድዶ ለተዋሕዶ መረጠሽ፡፡” በማለት የተረጎመው፡፡

የተወደዳችሁ ምእመናን ለበረከት ይሆነን ዘንድ ከአባቶቻችን ቅዱሳን ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ እመቤታችንን ካመሰገነበት የምስጋና ድርሰቱ አንዱን አንቀጽ እናንሣና ለአሁኑ እንሰነባበት፡፡

“ተፈሥሒ ኦ ወላዲተ እግዚእ ሐሤቶሙ ለመላእክት፡፡” የሚለው ቃል በቅዱስ ኤፍሬም የምስጋና ድርሰት ይገኛል፡፡ /የማክሰኞ ውዳሴ ማርያም/ ይህንን የምስጋና ድርሰት አባቶቻችን መምህራን እንዲህ ተርጉመውታል፡፡ “የመላእክት ደስታቸው የሚሆን ጌታን የወለድሽው ተፈሥሒ ደስ ይበልሽ፡፡ ለሊሁ ዓለሞሙ፣ ወለሊሁ ተድላሆሙ፣ ወለሊሁ ሀገሮሙ እንዲል፡፡ አንድም ሥጋዌውን ተልከው ለነቢያት የሚነግሩ መላእክት ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሣ በአጭር ቁመት በጸባብ ደረት ተወስኖ አይተውት፤ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ብለው አመስግነውት፤ በጣዕም ላይ ጣዕም በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላቸው ደስ ብሏቸዋልና፡፡ አንድም የመላእክት ደስታቸው የምትሆኝ ጌታን የወለድሽው ተፈሥሒ ደስ ይበልሽ፡፡ ንጽሕናዋን ቅድስናዋን እያዩ ደስ ይላቸዋልና ሐሤቶሙ ለመላእክት አለ፡፡”

እንግዲህ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ፡- “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን ወበከመ ሰማዕክሙ ዘንተ ቃለ ቅዳሴሃ ለማርያም ከማሁ ያስምዕክሙ ቃለ መሰናቁት ዘሕፃናት” እንዳለው፤ ይህንን የእመቤታችንን ምስጋና ውዳሴ ለመስማት ለማንበብ ያበቃን ፈጣሪያችን በቸርነቱ ብዛት ከጣዕሙ ብዛት አጥንትን የሚያለመልም የመላእክትን ምስጋና የሕይወትን ቃል ያሰማን፡፡

ከእመቤታችን ከወላዲተ አምላክ ከድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ ፍቅሯን በልባችን፣ ጣዕሟን በአንደበታችን ይሳልልን ያሳድርብን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment