Sunday 21 October 2012

ጾመ ጽጌ

ዲያቆን መልአኩ እዘዘው












የጾም ትርጓሜ
የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገሥት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል፡- ጾምሰ ተከልአተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ - ጾምስ በታወቀው ዕለት፣ በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ አንድም ጾም ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ይህም ኃጢአቱን ለማስተሰረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ሥራም ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ፍት.ነገ.ፍት. መ. አንቀጽ 15564፡፡ በዚህ መሠረት ጾም ማለት ከጥሉላተ መባልዕት /ሥጋ ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ እንቁላል እንዲሁም የአልኮል መጠጦች/ መታቀብ ነው፡፡
ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው፡፡ ለፈቃደ ሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ ሰው ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት ስንቅ ነው፡፡ ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣ የጽሙዳን ክብራቸው፣ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው፣ የጸሎት ምክንያት /እናት/፣ የእንባ መገኛ ምንጭ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡ /ማር. ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6/፡፡

የጾም ዓይነቶች
ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደምንረዳው ጾም በዓይነቱ በሁለት ሊከፈል ይችላል፡- የዐዋጅና የግል፡፡ የዐዋጅ ጾም በይፋ ለሕዝቡ ተነግሮ በአንድነት የሚጾም የትዕዛዝና የሕግ ጾም ነው፡፡ በ “በጽዮን መለከትን ንፉ፣ ጾምን ዐውጁ ጉባኤውንም ቀድሱ” /ኢዩ. 1፣ 1214/፡፡ በብሉይም ሆነ በሐዲስ ወቅታቸው /ወራቸውና ቀናቸው/ በየዓመቱ የሚታወቁ የዐዋጅ ወይም የሕግ አጽዋማት ነበሩ፡፡ አሉም፡፡ በብሉይ ኪዳን “ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- የአራተኛው ወር ጾም፣ የአምስተኛውም፣ የሰባተኛውም፣ የዐሥረኛውም፣ የሰባተኛውም፣ የዐሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሴትም በዓላት ይሆናል፡፡”  /ት .ዘካ. 8፣18፡19/
በሐዲስ ኪዳንም ፈሪሳውያን ከሳምንቱ ቀናት ውስጥ ሁለቱን /ሰኞንና ሐሙስን/ ወስነው እንደሚጾሙ  “ አንሰ እጸውም ሰኑየ መዋዕለ በኩሉ ሰናብት፣ እኔ በየሳምንቱ ሁለት ቀን እጾማሁ” /ሉቃ. 18፣12/ የሚል አስረጅ ይገኛል፡፡ በግብረ ሐዋርያት መጽሐፉ ቅዱስ ሉቃስ ስለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ ሲጽፍ   “ብዙም ጊዜ ካለፈ በኋላ የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበር” በማለት ያሰፈረው ቃል በዘመነ ሐዋርያት የተወሰነ የጾም ጊዜ መኖሩን ያረጋግጥልናል፡፡ / ግብ.ሐዋ.279131-3፡፡
በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሁሉ እንዲጾማቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ፣ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የዐዋጅ /የሕግ/ አጽዋማት አሉ፡፡ እነዚህም ዐቢይ ጾም /ጾመ ዐርባ/፣ ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/፣ ጾመ ፍልሰታ /ጾመ ማርያም/፣ ጾመ ነቢያት /የገና ጾም/፣ ዶመ ድራረ ጥምቀት /ገሃድ ወይም ጋድ/፣ ጾመ ሰብአነነዌ፣ ጾመ ድኅነት /የረቡዕና ዓርብ ጾም ናቸው ፡፡
እንዲህ ወራት ተወስኖለት በቁጥር የተወሰነ በጊዜ የተገደበ ይሁን እንጂ የዘለዓለም ሕይወትን ለመውረስ የሚረዳን የጽድቅ መሠረት፣ የገነት በር በአጠቃላይ የክርስቲያች ኑሮ ስለሆነ ከተዘረዘሩት የሕግ አጽዋማት በላይ ከዓመት እስከ ዓመት የሚጾሙ በገዳም፣ በበረሃ ያሉ መነኮሳትና ባሕታውያን አሉ፡፡ “ስለ ጽድቅ የሚራቡ፣ የሚጠሙም ብፁዓን ናቸው፣ እነርሱ ይፀግባሉና፡፡” /ማቴ.56፤ ኢሳ 4117፣ 551/፡፡
አበው  “ቢቻላችሁስ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ፣ ለድኾችም ምጽዋት ስጡ” /ፍትሐ ነገስት .ፍ.መ. 15580/ በማለት እንዳዘዙት ጾምን ቢያዘወትሩ ለስርየተ አበሳ፣ ሥጋን ለመጎሰምና ለነፍስ ተግባር ለማሠልጠን ይመቻል፡፡  “ ሰው ይረባኛል ይመቅመኛል ብሎ አብዝቶ ከመጾሙ የተነሣ አንጦንስን መቃርስን እንዲሁም መላእክትን ይመስላል” ሲሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡
ይህም ወደ ሁለተኛው የጾም ዓይነት ማለት ወደ የግል ጾም ይወስደናል፡፡ የግል ጾም እግዚአብሔር ኃይሉንና ብርታቱን የሰጣቸው ምእመናን በግል /በስውር/ የሚጾሙት ነው፡፡ አንድ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር የሚፈልገው ነገር ሲኖር፣ ራሱን ለመግዛት ይችል ዘንድ እንዲሁም ንስሐ ገብቶ የንስሐ አባቱ ሲያዝለት በግሉ ይጾማል፡፡ ይህም ከጥንት ጀምሮ የነበረ ሥርዓት ነው፡፡ ለአብነት ያህል ሊቀ ነቢያት ሙሴን /ዘጸ.24፣18/፣ ነቢዩ ዳንኤል /ት.ዳን. 9፣3/፣ ነህምያን / ነህ.9፣1-4/ በሐዲስ ኪዳንም ቅዱስ ጳውሎስንና ቅዱስ ጴጥሮስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ /ግብ.ሐዋ.10፣10፣ 2 ቆሮ. 6፣5፣11፣27/፡፡ የግል ጾም ከዐዋጅ ጾም ጋር አንድ መሆን አይገባውም፡፡ የግል ጾም የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡
የንስሐ ጾም ምእመናን ከመምህረ ንስሐቸው ጋር ተመካክረው ንስሐ ገብተው በአንቀጸ ንስሐ መሠረት ቀኖና ሲሰጣቸው የሚጾሙት ጾም ነው፡፡ ቀኖናውን የሚፈጽሙት ማንም ሳያውቅባቸው በስውር ይሆናል፡፡ አንዳንዶች በንስሐ አባቱ የታዘዘ ምእመን ሕጋዊ መመሪያ ተቀብሎ ስለሚጾም ራሱን መደበቅ አያስፈልገውም ቢሉም ጸዋሚው መጾሙን ምናልባት ከቅርብ ቤተሰቦቹ ውጭ ሌላ ሰው አያውቅበትም፣ ማሳወቅም የለበትም፣ ተሰውሮ ይጨርሰዋል እንጂ፡፡ በንስሐ አባቱ የተሰጠውን ቀኖና እስኪፈጽም ፈጣሪው የቀደመ ኃጢአቱን ይቅር እንዲለው ሥርየት እንዲሰጠው በእንባ ይማፀናል፡፡ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ መዝ.61-10፡፡ የግል ጾም በተለያዩ ምክንያት ( ለምሳሌ በወሊድ ፤ በሕመም ወዘተ) የአዋጅ አጽዋማትን መጾም ላልቻሉ በአዋጅ አጽዋማት ፈንታ በንስሐ አባት የሚሰጥ ትእዘዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም የንስሐ ጾም የብይን ጾም ይባላል፡፡
የፈቃድ ጾም በሌላ አጠራር የትሩፋት ጾም  በመባል ይታወቃል፡፡ በዝግ ወይም በማኅበር ሊፈጸም ይችላል፡፡ እግዚአብሔርን በትጋት የሚያገለግሉ ምእመናን በግል ወይም በማኅበር፣ በገዳም የሚኖሩ አባቶች በአንድነት ስለሚከተሉት ምክንያቶችና ስለ መሰሏቸውም የፈቃደ ጾም ይጾማል፡፡
Ø በግልና በቤተሰባዊ ሕይወታሕይወታቸው የገጠማቸው ችግር ካለ እንዲወገድላቸው፣ በሚኖሩባት አገርና በቤተክርስቲያናቸው ዙሪያ ያላቸው እክል እንዲርቅላቸው፣
Ø ክቡር ዳዊት “ነፍሴን በጾም አስመረርካት” እንዳለ ራሳቸውን መግዛት ይችሉ ዘንድ ነፍስን በሥጋ ላይ ለማሠልጠን
Ø በጥቂት ሲለምኑት አብዝቶ የሚሰጥ እግዚአብሔር ምሥጢር እንዲገልጥላቸው /ዳን. 10፣14/
Ø የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ የቅዱሳንን መከራ እያሰቡ በረከታቸውን ለመሳተፍ፣ ከኃጢአት ለመንጻት የሚሉት ናቸው፡፡

የፈቃድ ጾም ቅድመ ዝግጅት
በስውር ለመጾም የሚያስብ ሰው ሊያደርገው የሚገባው ቅድመ ዝግጅት አለ፡፡ በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ቢጀምረው ግን በመሐል አቋርጦ ሊተወው ይችላል ወይም ያሰበውን ሳያገኝ ይቀራል፡፡ ዝግጅቱ በብዙ መልኩ ነው፣ ለአብነት ያህል፡-
·        ከንስሐ አባት ጋረ መመካከር ይገባል፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር የሚመራ በምክረ ካህን የሚኖርና የሚጓዝ ሰው ፈተና ቢገጥመው መከራ ቢደራረብበት እንዴት ማለፍ እንዳለበት ስለሚያውቅ አይረበሽም፣ ይታገሣል እንጂ፡፡ ስለዚህ በግሉ ጾም ለመያዝ የሚያስብ መጀመሪያ ከንስሐ አባቱ ጋር ቢነጋገር እጅግ የተሻለ ነው፡፡ አባቱ በጾሙ ወቅት እንዲያስቡት እንዲጸልዩለት ቢያደርግ ፈተናውን ተቋቁሞ ጾሙን መጨረስ ይችላል፡፡
·        ጸዋሚው ለንስሐ አባቱ እንዲሁም ግድ ማወቅ ላለባቸው ቤተሰዎች ብቻ ካልሆነ ላገኘው ሰው ሁሉ ሱባኤ ልጀምር ስለሆነ አትርሱኝ እያለ መንገርና ጾሙን ማወጅ የለበትም፡፡ ውዳሴ ከንቱ ሊያመጣበት ይችላልና፣ ለሰው ሁሉ ሲነግር የሰማ ጠላት ዲያብሎስም እንቅፋት ያበዛበታል ፈተና ያከብድበታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ ይህን በተመለከተ ሲናገር  “. . . ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፣ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል፡፡” ብሏል፡፡ ማቴ 6፡18፡፡ ስለዚህ በግሉ የሚጾም ሰው ለማንም ሳይነግር /ሳያውጅ/ መጾም ይገባዋል፡፡ ቆሎ ዘግኖ ወይም በሶ ብቻ በመብላት መጾሙን፣ አብዝቶ መስገድ መጸለዩን መናገር የለበትም፡፡ ቢናገር ግን ድካሙን ሁሉ ከንቱ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ በምድር ያገኘው የሰዎች ወዳሴ እግዚአብሔር ያዘጋጀትን ጸጋና ረድኤት ያስቀርበታልና፡፡
·        በፈቃዱ ሱባኤ መያዝ /መጾምና መጸለይ/ የሚፈልግ ሰው ዐቅሙን የሚያውቅ መሆን አለበት፡፡ የጾሙን ጊዜ መወሰን ያለበት ያለውን ጥንካሬ፣ ልምዱንና ጽናቱን ገምግሞ ሊሆን ይገባል፡፡ ጀማሪ ክርስቲያን  “በዋሻ ዘግቼ በቀን አንድ ጊዜ ጥሬ ቆርጥሜ መቶ ሃምሳ መዝሙረ ደግሜ” እጾማለሁ ቢል ከዐቅሙ በላይ ሆኖበት፣ ጥብዓት ጎድሎት፣ ትዕግሥት አንሶት ሊያቋርጠው ይችላል፡፡ ስለዚህ እንደ ዐቅሙ መጾም መጸለይ ይገባዋል፡፡
·        ጸዋሚው የታወቀ ዓላማ ሊኖረው በሚያሳልፋቸው የጾም ዕለታት እግዚአብሔር አምላኩ እንዲያደርግለት የሚጠይቀውን ጥያቄ ጠንቅቆ ማወቅና ማዘጋጀት ይገባዋል፡፡ ብዙ መነኮሳት፣ ባሕታውያንና ምእመናን በፈቃድ የሚጾሟቸው የታወቁ ጊዜያት አሉ፡፡ እኒህም የጽጌ ጾም /ጾመ ጽጌ/ ና በጳጉሜን ወር የሚጾመው “ጾመ ዮዲት” ናቸው፡፡

ሀ/   “ጾመ ጽጌ”
ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ያለው አንድ ወር ከዐሥር ቀን ወይም 40 ቀን ወርኃ ጽጌ፣ ዘመነ ጸጌ፣ ተብሎ ይጠራል፡፡ በነዚህም ቀናት በየቤተክርስቲያኑ የሚነበቡ ምንባቦች፣ የሚዘመሩት መዝሙሮች፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚቆመው ማኅሌት በጠቅላላው የሚነገረው ስብሐት እግዚአብሔር ሁሉ ሰማይ በከዋክብት ምድር በጽጌያት አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡
ወርኃ ጽጌ ለሚከናወነው መንፈሰዊ አገልግሎት መነሻው    “መልአኩ ሕፃኑንና እናቱን ወደ ግብፅ ይዘሃቸው ሽሽ፣ የሕፃኑን ነፍስ ሊገድሉት ይፈልጋሉና” ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሠረተ ዮሴፍም ሕፃኑንና እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ ወደ ግብፅ መሰደዱና እመቤታችንና ሕፃኑ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ /ራእይ.12፣6/ ወደ አገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው፡፡ /ማቴ. 213-23፣ ት.ኢሳ.191፣ እንባቆም 36-7፣ መዝ.833/፡፡
ይህንንም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡ አባ ጽጌ ብርሃን ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኝ ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመለሰ በሚያስረዳው ድርሰታቸው እንዲህ በማለት ገልጸውለታል፡፡  “ አፈወ ሮማን ማርያም ጽጌ ቀናንሞ ወአበሜ፣ እስከ ተጸምሐየየ በጾም ዘመልክዕኪ ጊዜ ድክታሜ፣ እምተመነይኩ ተሳትፎ ከመ አኅትኪ ሰሎሜ፣ ወፍሥሓኪ ዘአልቦ ፍጻሜ”፡፡ ሲተረጎምም የሮማን ሽቱ የቀናንሞ አበባ የምትሆኚ ማርያም ሆይ፣ በርሃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪጠወልግ ድረስ በስደትና በልቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እኅትሽ እንደ ሰሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፤ በዚህ ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር፡፡
እንዲሁም አባ አርክ ሥሉስ በስደቷ የደረሰባትን ኀዘን ፣ ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት   ‘ሰቆቃወ ድንግል” በሚለው ድርሰታቸው እንዲህ አሉ፣ ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሸሽ ጊዜ የደረሰብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንደ ጎበጎቡ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር”፡፡ 


ማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር

 የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡
የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ገድል የጽጌን ጾም አስመልክቶ የሚከተለውን ይተርካል፣ “አቡነ ዜና ማርቆስ የምሁርን ሕዝብ አስተምረውና አሳምነው ካጠመቁ በኋላ እንደገና ለማስተማር ወደ ይፋት ሄዱ፡፡ በዚያም ክርስቶስ ሥጋ ለብለሶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰለኛ ኃጢአት ተሰቅሎ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተነሣ እያሉ ሲያስተምሩ አንድ አይሁዳዊ ሰማ፡፡ ይህም አይሁዳዊ እንዴት እነዲህ እያለ ያስተምራል ሲል ተቃውሞ አቀረበባቸው፡፡ እርሳቸውም የብሉይና ሐዲስ ዐዋቂና ብልህ ስለነበሩ የሚከተለውን ጥቅስ እየጠቀሱ ያስረዱት ጀመር፡፡”

“ትወዕዕ በትር እምሥርወ እሴይ፣ ወየዓርግ ጽጌ እምጒንዱ”፣ ትርጓሜውም “ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች ከግንዱም አበባ ይወጣል ያቆጠቁጣል” ማለት ነው፡፡ በትር አመቤታችን ድንግል ማርያም ስትሆን ጽጌ ደግሞ ከእርስዋ የተወለደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲሉ አቡነ ዜና ማርቆስ በትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 111  ያለውን ትርጓሜውንና ምሥጢሩን ዘርዝረው ባስረዱት ጊዜ አይሁዳዊው አምኖ ትምህርታቸውን ተቀበለ፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስም ሐዲስ ኪዳን አስተምረው አሳምነው ካጠመቁት በኋላ አመነኮሱት፣ ስሙንም ጽጌ ብርሃን ምሁረ ኦሪት ስለ ነበር መጻሕፍተ ሐዲሳትን ለማጥናት ምቹ ሆነለት፣ ቀጥሎም ከርሳቸው ጋረ እየተዘዋወረ ወንጌል ያስተምር ጀመር፡፡
ይህንንም ከፈጸመ በኋላ እንደ መዝሙረ ዳዊት መቶ ሃምሳ አድርጎ ማኅሌተ ጽጌ ደረሰ፡፡ አባ ጽጌ ብርሃን ይህንን በደረሰበት ጊዜ የወረኢሉ ተወላጅና የደብረ ሐንታው አባ ገብረ ማርያም አማካሪው ነበር፡፡ ድርሰቱንም ሲደርስ ቤት እየመታና በአምስት ስንኝ እየከፋፈለ ነው፡፡ አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም መስከረም 26 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ማኅሌት ጽጌ ለመቆምና የጽጌን ጾም ለመጾም በየዓመቱ በደብረ ብሥራት እየመጡ ይሰነብቱና ቁስቋምን ውለው ወደየበዓታቸው ይመለሱ ነበር፡፡
ይህም ማኅሌተ ጽጌ ድርሰት በሰምና ወርቅ የተደረሰ ሆኖ አበባን ሰም፣ ጌታንና እመቤታችንን ወርቅ እያደረገ ስለሚናገር ለሚያነበውና ለሚጸልየው እጅግ ያስደስታል፡፡
እንግዲህ ከላይ ከቀረበው የአባታችን የገድል ክፍል ለመረዳት እንደሚቻለው አባ ጽጌ ማኅሌት መቆም ወቅቱንም በፈቃዳቸው መጾም  ጀምረዋል፡፡ ዘመኑም በ14ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው፡፡
ከዚያ ወዲህ ግን ጥቂት በጥቂት እያለ አብያተ ክርስቲያናት በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ጀመሩ፡፡ ጥቂት መነኮሳትና አንዳንድ ምእመናንም በገዛ ፈቃዳቸው ወቅቱን መጾም ያዙ፡፡ በዘመናችን በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ስለ ተለመደ ከማታው በሦስት ሰዓት ይደወላል፡፡ ሴቱ ወንዱ፣ ትንሹም ትልቁም ይሰበሰባል፣ ማኅሌተ ጽጌ እየተዜመ፣ አስፈላጊ የሆነው በጸናጽል በከበሮ እየተመረገደና እየተወረበ እየተሸበሸበ እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ ተቁሞ ይታደራል፡፡ የጽጌ ጾም የውዴታ /የፈቃድ/ እንጂ የግዴታ አይደለም፡፡
የእመቤታችንን ስደት በማሰብ ከትሩፋት ወገን የሚጾም ስለሆነ ምእመናን ሁሉ እንዲጾሙት አይገደዱም የሚጾመው የማይጾመውን ለምን አልጾምክም ብሎ ሊፈርድበት፣ ለራሱም እየጾምኩ ነው ብሎ መናገር አይገባውም፡፡ የፈቃድ መሆኑንም የሚያሳየው ይኸው ነው፡፡ የማይጾመውም በልቡ ያመሰግናል፣ስደቷን እያሰበ ማኅሌቷን እየዘመረ ያሳልፋል፡፡
ለ. ጾመ ዮዲት
ይህን ጾም በሀገራችን ምእመናን ጾመ ጳጉሜን በማለት ይጠሩታል፡፡ እንደ ጽጌ ጾም የታወቀ ባይሆንም በዓመቱ መጨረሻ ወር በጳጉሜን የሚጾም ነው፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ የፋርስ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ፣ ድንበር አሰፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ2፣2-7፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12 ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12 ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ አገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ፡፡
የእሥራኤል ልጆችም ሆሎፎርኒስ የአሕዛብን አገር እንዳጠፋና ንብረታቸውን እንደዘረፈ ሰምተው ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስና ሰለ ንዋያተ ቅድሳት መርከሰ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው ከቤተ መቅደሱ በር ወድቀው አለቀሱ፡፡ እግዚአብሔር ልመናቸውን ሰምቶ ከዚህ ጥፋትና ወረራ እንዲያድናቸው እንዲጠብቃቸው መሠውያውንም ሳይቀር ማቅ አለበሱት፡፡ ዮዲ. 42-15፡፡
እብሪተኛው ቢትወደድ ግን የሕዝበ እሥራኤልን ምንጫቸውንና ውኃ አስቀድሞ በመያዝ እንዲቸገሩና ወደው ፈቅደው እጃቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ የውኃውን ጉድጓድ ተቆጣጥሮ በሠራዊቱ አስጠበቀ፡፡ በመሆኑም የእሥራኤል ልጆች በውኃ ጥም ከመቸገርና ከመሞት ይልቅ እጃቸውን ለጠላት ለመስጠት ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ዖዝያን የአባቶቻቸው አምላክ መልስ እስኪሰጣቸውና ቸርነቱን እስኪመልስላቸው መከራውን በትዕግሥት እንዲቀበሉ ስለመከራቸው ጸኑ፡፡ ዮዲ. 710-32፡፡
ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም፣ በቀኖና፣ በትኅርምት፣ በኀዘን፣ በጸሎት ተወስና ትኖራለች “ብንችል እንዋጋለን ባንችል እንገብራለን” ሲሉ እሥራኤልን ሰምታቸው ፈጣሪያችሁን ለምን ትፈታተኑታላችሁ ያድነናል አትሉምን? ብላ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትቢያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡
የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ ቸር አምላክም ሕዝቡን የሚያድንበትን ዕውቀትና ጥበብ ግብር በገባች በሦስተኛ ቀን ገለጸላት፡፡ ዮዲ. 82፡፡ ዮዲት እጅግ መልከ መልካም ፍጹም ደመ ግቡ ስለነበረች እግዚአብሔር በሰጣት አካል የወገኖቿን ጠላት አስታ የምታጠፋበትን ዘዴ አዘጋጀች፡፡ በመጀመሪያ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች፡፡ ከዚያም  “ወዴት ትሔጃለሽ አትበሉኝ አምላክ እሥራኤል ይከተልሽ ብሉኝ”ብላ የኀዘን ልብሷን ጣለች፡፡ ሰውነቷን ታጠበችና ሽቱ ተቀባች፣ ባሏ በሕይወት ሳለ የምትለብሰውን የክት ልብሷን ለበሰች፣ የሚመለከቷትን ሰዎች ሁሉ እስክታስት ድረስ ፈጽማ አጌጠች፡፡ ዮዲ.102-3፡፡ ስትጨርስም እግዚአብሔር በመልክ ላይ መልክ ጨምሮራት ለመንገድ ስንቅ የሚሆናትን ወይንና የስንዴ አምባሻ ብላቴናዋን አስይዛ ከእየሩሳሌም ቅጥር ወጥታ የፈረስ ሰራዊት ወዳለበት ሄደች፡፡
 ሸማ አጣቢዎች አገኟትና  “ ዛሬስ እስራኤል መዋጋት ቢሳናቸው አንዳንድ እያሉ ወባት ሊገቡ መጡብን?” ብለው ለእኔ ትገባለች ለእኔ ትገባለች እያሉ ተሻሙባት፡፡ የንጉሥ ጃንደረባ ጋይ የሚባል ይህችስ ለጌታዬ ትገባለች አለ፣ ለምን እንደመጣች ጠይቀዋት ለመልካም ነገር እንደመጣች ሲረዱ ከጦር አበጋዙ አደረሷት፡፡ ዮዲ.1012-22፡፡ እርሱም የጾመኛ ምቀኛ እንዲሉ ለምን መጣሽ ቢላት እስራኤል ሊገቡ ጥቂት ቀርቷቸዋል፣ እርስት ሄዶብኝ እንድትመልስልኝ አስቀድሜ ደጅ እጠናለሁ ብዬ መጣሁ አለችሁ፡፡ እርሱም ወገን ለመርዳት እንደመጣች ተረዳ፣ የተለበጠ ነጭ ሀር ልብስ በተነጠፈበት በድንኳኑ እንዲያስቀምጧት እርሱ ከሚበላው ምግብ እንዲሰጧት አዘዘ፡፡ እርሷ ግን የአህዛብ ምግብ በልታ እንዳትረክስ በቂ ስንቅ የያዘች መሆኗን ገልጻ በፈለገችበት ጊዜ ለመውጣትና ለመግባት የምትችልበትን ሁናቴ አመቻቸች፡፡
አሕዛብ በዚህ ቀን ተወልደን ከዚህ ማእረግ ደርሰን ከጨለማ ወደ ብርሃን ከጠባብ ወደ ሰፊ የወጣንበትን ሲሉ የተወለዱበትን ቀን ያከብራሉ፡፡ በአንዲትም ዕለት ቢትወደዱ የአሽከሮች የምሣ ግብዣ አድርጎ ሲያበላ ሲያጠጣ ያችን እብራዊት ጥሩ ብሎ አስጠርቶ ከፊቱ አስቀምጦ ሲበላ አብዝቶ ሲጠጣ ውሏል፡፡ ዮዲ. 121-20፡፡ ከዚያም አሽከሮችን ከሁሉ አስወጥቶ ድንኳኑን ቆልፎ እንደተኛ ከባድ እንቅልፍ ያዘው ዮዲትም በሃያሉ አድረህ ሥራ ብትሠራ አትመሰገንም ነገር ግን በእኔ በደካማይቱ አድረህ ሥራ ብትሠራ ትመሰገናለህ እያለች ከፀለየች በኋላ ከራስጌው ያለውን ሰይፍ አንስታ የራስ ጠጉሩን ይዛ አንገቱን ቆርጣ በድኑን ከመሬት ጥላ ቸብቸቦውን በአቁማዳ ቋጥራ ለብላቴናዋ አሸክማ ግንዱን በታች ገልብጣ ዙፋኑን በላይ  አድርጋ ወደ ሃገሯ ተመለሰች፡፡ ዮዲ13.1-10፡፡
ሕዝበ እሥራኤል በዚህ ድርጊቷ እጅግ ተደነቁ፣ ጠላታቸውን በእጃቸው የጣለላቸውን አግዚአብሔር አምላካቸውንም አመሰገኑ፡፡ በኋላም የሆሎፎርኒስን ራስ በተራራው ላይ ሰቅለው መዋጋት ጀመሩ፡፡ አረ ዛሬስ እሥራኤል ወንዳ ወንድ ሆኑብን ይህቺ ዕብራዊት የሌሊቱ አልበቃ ብሏት ቀኑንም ልትደግመው ነውን? ሒደህ ንጉሣችንን አስነሣው ብለው ብላቴና ቢልኩ ግንዱ በታች ዙፋኑ በላይ ሆኖ አገኘው፡፡ አውራ የሌለው ንብ አለቃ የሌለው ሕዝብ መቆም አይሆንለትምና ይህች ዕብራዊት እንዴት ተጫወተችብን ብለው ሸሽተዋል፡፡ እግር በራስ እየሆኑ አልቀዋል፡፡ እስከዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
 ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጦምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንንና ፈቃደ ስጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው በጳጉሜ ወር ይጾማሉ፡፡ ኃጢያታቸውን ለንስሐ አባታቸው ተናገረው ተናዝዘው ቀኖና ተቀብለው የሚጾሙም አሉ፡፡ በሌላም በኩል በጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብባት በመሆንዋ ያን እያሰቡ የሚጾም አያሌ ናቸው፡፡ ጳጉሜን የዓመታት መሸጋገሪያ እንደሆነች ምጽአትም ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ያሳትፈን 

No comments:

Post a Comment