Wednesday 30 November 2011

“ታቦተ ጽዮን” ፤ “ኅዳር ጽዮን“ ፤ “አክሱም ጽዮን “ ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለት - ዲያቆን መልአኩ እዘዘው



 ክፍል አንድ 


       የታቦተ ጽዮን መንበር -አክሱም











የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው 
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት አንዱ 
“ኅዳር ጽዮን” ሲሆን የሚከበረውም ኅዳር 21 ቀን ነው፡፡
የበዓሉን አከባበር ፤ ጥንተ ታሪኩን፤ ንግስት ሳባ ፤ቀዳማዊ ምኒልክና 
ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮችን በተከታታይ ክፍሎች እንመለከታለን፡፡ 


ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  “ታቦተ ጽዮን” 
የፈጸመችውን ልዩ ልዩ ተአምራት ለምእመናን እያስተማረች 
በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት 
በማድረግ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና 
አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን 
ጽላት /ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡  
“ታቦተ ጽዮን” የሚለውንም ስያሜ ያገኘችው ጽዮን ተብላ 
በምትጠራው የእስራኤል ከተማ ስም ነው፡፡ 
ጽዮን ማለት ተፀወነ፡- ተጠጋ፣ ተማጠነ ማለት ነው፡፡ ክቡረ ዳዊትም ጽዮንን 
አምባ፣ መጠጊያ አድርጎ ብዙ ጠላቶቹን ተዋግቶ አሸንፎ ድልን ተጎናጽፏል፡፡

አጼ ፋሲል በ16ኛው ክፍለዘመን ያሰሩት ቤተክርስቲያን ከፊት ለፊት እና በጎን ሲታይ
ጽዮን የተባለችው የታላቁ የዳዊት ከተማ የተገፉና የተበደሉ ሕዝቦች ሁሉ 
እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት፣ ተሰብስበው የሚሰነብቱባት ከተማ ስለነበረች፣
 ጽላተ ሙሴም በዚያ ስለነበረች በርሷ ተማጽነውም ችግራቸው ሰለሚቃለል
 ታቦቷ “ታቦተ ጽዮን” ተብላለች፡፡

ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ በራእዩ “በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተች፡፡ በውስጧም ያለችው ታቦተ ሕግ ታየች፡፡” ራእይ. 11 ሚ 19 በማለት የተናገረውን ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ ሲተረጉመው “በሥላሴ ጸዲል በሥላሴ ብርሃን የተመላች ስመ ሥላሴ የተጻፈባት ታቦት በኢየሩሳሌም ሰማያዊት አለች፡፡ በዚህች ታቦት ላይ ከፍጥረተ ዓለም በፊት ስመ እግዝእትነ ማርያም ተጽፎባት ነበር፡፡ ቅድመ ዓለም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመፈጠሯ በፊት በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖረ ነበር የሚለው መሠረቱ ይህ ነው” ብሏል፡፡ ታቦተ ጽዮን የምትኖርበትን ድንኳን ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንዲሠራ እግዚአብሔር ነግሮታል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሲናገር “ደብተራ ኦሪትን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት አርአያና ምሳሌ እንዲሠራ እግዚአብሔር አሳይቶታል፡፡ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሁለንተናዋ ከብርሃን የተሠራች ናት፡፡ የኢየሩሳሌም ሰማያዊት ቅርጽም ደብተራ ኦሪትን ትመስላለች፡፡” ይላል፡፡ ሕዝቡም ከፈጣሪያቸው ጋር ቃል ኪዳን ገብተው በታቦተ ጽዮን አማካኝነት ሲያመሰግኑ ኑረዋል፡፡
ታቦተ ጽዮን እግዚአብሔርን ለሚያምኑ፣ ሕጉን ትእዛዙን ለሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ ልዩ ልዩ ተአምራትን እንደፈጸመች ከቅዱስ መጽሐፈ እንረዳለን፡፡ እስራኤላውያን ሕጉን ሲጠብቁ ትእዛዙን ሲፈጽሙ እግዚአብሔር በታቦተ ጽዮን እያደረ ይረዳቸውና ጠላቶቻቸውንም ድል ያደርጉ ነበር፡፡ ሕጉን ሲያፈርሱ ደግሞ በጠላቶቻቸው ይሸነፉ ነበር፡፡
አጼ ኃይለሥላሴ ያሰሩት ቤተክርስቲያን - አክሱም
በዚያ ዘመን ኤሊ የሚባል ሊቀ ካህናት ነበር፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ እድሜውም 98 ዓመት ነበር፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የአባታቸውን ምክር አቃልለው የማይገባ ኃጢአት ሠርተው አምላካቸው እግዚአብሔርን አሳዘኑ በራሳቸው ፈቃድ ተጉዘው ሕገ እግዚአብሔርን ጣሱ፡፡ በሕዝቡም ላይ የሚያደርሱት በደል እየጨመረ ሔደ፡፡
አፍኒንና ፈንሐስ እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት በረድኤት ስለተለያቸው ፍልስጥኤማውያን በጠላትነት ተነሡባቸው፡፡ እስራኤላውያን ከኤሊ ልጆቸ ጋር ሆነው በአንድነት ታቦተ ጽዮንን ይዘው ለጦርነት ወደ ፍልስጥኤም ዘመቱ፡፡ ጦርነትም ገጠሙ ታላቅ ግድያም ሆነ፡፡ በጦርነቱ አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ፡፡ ታቦተ ጽዮንም በኤሎፍላውያን እጅ ተማረከች፡፡ ሕዝቡም በጦርነት አለቁ፡፡ ከጦርነቱ ያመለጠ አንድ ሰው ወደ ኤሊ ሄዶ እስራኤላውያን ተሸንፈው መሸሻቸውን፡ ሁለቱ ልጆቹ አፍኒንና ፊንሐስ መሞታቸውን ታቦተ ጽዮንም መማረኳን ነገረው፡፡
ኤሎፍላውያንም ታቦተ ጽዮንን ማርከው ከወሰዷት በኋላ ዳጎን ከተባለው ጣዖታቸው በታች አስቀመጧት፡፡ በማግስቱ የዳጎን አገልጋዮች መጥተው ቢያዩአት ፣ ዳጎን ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት፡፡ አንስተው አቁመውት ሔዱና በማግስቱ መጥተው ቢያዩት በግንባሩ ወድቆ እጆቹ ተለያይተው ጣቶቹም ተቆራርጠው ደቀው በወለሉ ላይ ተበታትነው ነበር፡፡ ታቦተ ጽዮን ግን ምን ጉዳት ሳይደርስባት ከላይ ሆና አገኙአት፡፡ አገልጋዮቹም ታቦተ ጽዮን ያደረገችውን ተአምር በማድነቅ ዳጎንን በመናቅና በማቃለል ከዚያ ቀን ጀምረው ከቦታው ፈጽመው አልደረሱም፡፡ 1ኛ ሳሙ 5፤1-7፡፡ ሕዝቡም በሰውነታቸው ላይ እባጭ እየወጣባቸው ሲገድላቸው ሌሎቹንም በሚያንቀጠቅጥና በሚጥል በሽታ እያሰቃያቸው፣ እህላቸው በአይጥ፣ እንስሶቻቸው በበሽታ አለቁባቸው፡፡
ታቦተ ጽዮን በኤሎፍላውያን ላይ እንዲህ ያለ ተአምር እየፈጸመች በፍልስጥኤም አገር ለሰባት ወራት ቆይታለች፡፡ ከሰባት ወራት በኋላ ኤሎፍላውያን ታቦተ ጽዮንን ወደ ሀገሯ ለመመለስ ወርቅ በሳጥን አድርገው በሠረገላ ጭነው በላሞች እያስጎተቱ ወደ ሀገሯ ሰደዷት፡፡ እስራኤላውያን የታቦተ ጽዮንን መመለስ በሰሙ ጊዜ በዕልልታ በሆታና በዝማሬ ተቀብለው አሚናዳብ ቤት አስገቧት፡፡ በዚያም ሃያ ዓመታት ኑራለች፡፡ የአሚናዳብ ቤት በታቦተ ጽዮን ምክንያት ተባርኮለታል፡፡ 1ኛ ሳ. 7፤2፡፡
ንጉሥ ዳዊት ታቦተ ጽዮን ወደ ከተማው በመጣች ጊዜ ከዙፋኑ ተነስቶ እየዘመረ በክብርና በምስጋና ተቀብሏታል፡፡ ብዙ መስዋዕትም ተሰውቷል፡፡ 2ኛ ሳሙ 6፤14፡፡ ታቦተ ጽዮን እስከ ንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ድረስ በድንኳን /በደብተራ ኦሪት/ ከተቀመጠች በኋላ በንጉሡ ሰሎሞን በተሠራው ቤተ መቅደስ ገብታለች፡፡ 1ኛ ነገ. 8፤1-12፡፡
የንግሥተ ሳባ ጉዞ ወደ ኢየሩሳሌም
ከጌታችን ልደት በፊት በ1ሺ ዓ.ዓ. በኢትዮጵያ የነገሠችው ንግሥት ሳባ ሦስት ስም አላት፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ 10፤1-10 እና በ2ኛ ዜና 9፤1-8 ላይ “ሳባ” በማለት ትጠራለች፡፡ በክብረ ነገሥት ደግሞ  “ማክዳ” ተብላለች፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ትምህርቱ “ንግሥት አዜብ” ብሏታል፡፡ ማቴ 12፤42፡፡ አዜብ ማለት ደቡብ ማለት ሲሆን ኢትዮጵያ በድሮ ግዛትዋ ለእስራኤል ደቡብ ነበረች፡፡ ጌታ ንግሥት አዜብ ያላትም ለዚህ ነበር፡፡ ይህንን ቃል ከእርሷ በኋላ 1500 ዓመት ቆይተው የተነሱት የኢትዮጵያ ነገሥታት ሳይቀሩ ይጠቀሙበት እንደነበር የቤተ ክርስቲያን መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
ስለ ንግሥት ሳባ ኢትዮጵያነት የሚያስረዱ የተለያዩ ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ከጥንታውያን የታሪክ ጸሐፍት መካከል የሚቆጠረው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ስለዚህችው ንግሥት “በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያና የግብጽ ንግሥት የነበረችው” በማለት ነበር የጻፈው፡፡ ላዕላይ ግብጽ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ግዛት እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ የግብጻውያን ትልቁ የታሪክ መዝገብ የሆነው የፓትርያርኮች ታሪክም እንዲህ ይላል “የታላቁ ሀገር አቢሲኒያ ንግሥት እርስዋም ንግሥት ሳባ የምትባል የደቡብ ንግሥት፣ ወደ ዳዊት ልጅ ሰሎሞን መጣች፡፡” ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም  በኢትዮጵያችን ከንግሥት ሳባ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ የአርኪዎሎጂ /የከርሰ ምድር ጥናት/  ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡
የንግስት ሳባ ቤተመንግሥት በአርኪዎሎጂ የተገኘ - አክሱም
የንግሥተ ሳባ ትውልድ ቦታ፡- በሰሜን ደንገሎ፣ በደቡብ ፎካደ በተባሉ በሁለት ተራሮች መካከል የሚገኝ ሲሆን ስሙም  “ጎሎ ማክዳ” ይባላል፡፡
የንጉሥ ምኒልክ አንደኛ መቃብር፡- አክሱም ከተማ በስተምዕራብ 2 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በ1906 የደች ልዑካን የአርኪዎሎጂ ጥናት በሚያደርጉበት ወቅት ከምድር ውስጥ የተቀበረ ቤት ውስጥ የንጉሥ ምኒልክን ዐጽም ያገኙ ሲሆን የአክሱም ጽዮን ካህናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር እንዳሳረፉት ይታወቃል፡፡
በ13ኛው መ/ክ/ዘመን የነበሩት የአክሱም ንቡረ ዕድ ይስሐቅ ከተለያዩ ምንጮች ክብረነገሥትን ሲያዘጋጁ እጅግ ታላቅ ቦታ ከሰጡዋቸው ታሪኮች መሐል አንዱ የንግሥት ሳባ ታሪክ ነው፡፡ ንግሥት ሳባ እግዚአብሔርን በመፍራት በመልካም ሁኔታ ሕዝቡን ታስተዳድር ነበር፡፡ በወቅቱ በእስራኤል ላይ ነግሦ የነበረውን የሰሎሞንን ጥበብ በጆሮ መስማት ብቻ በቂ ሆኖ ስላላገኘችው በዓይን አይቶ መረዳት የበለጠ መሆኑን ተገነዘበች፡፡
ለንግሥት ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ምክንያት የሆናት ታምሪን የተባለው ነጋዴ ነው፡፡ ይህ ነጋዴ በኢየሩሳሌም በሚቆይበት ጊዜያት ብዙውን  ጊዜ የሚያሳልፈው የሰሎሞንን ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብ በማየት ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በሚመለስበትም ጊዜ እየዘረዘረ ለንግሥት ሳባ ይነግራትና ያስረዳት ስለነበር፤ ንግሥት ሳባ ከዚሁ ነጋዴ በሰማችው ዜና የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ለማየት ጓጓች፡፡ በዚህም የተነሣ በታምሪን መሪነት ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፡፡ እግዚአብሔርም መንገዱን አቀናላት፤ ያለአንዳች መሰናክል ተጉዛ ኢየሩሳሌም ደረሰች፡፡ ለታቦተ ጽዮን ክብርና ለንጉሥ ሰሎሞንም ገጸ በረከት አቀረበች፡፡ 1ኛ ነገ. 10 ሚ 1-13፡፡
ንጉሥ ሰሎሞንም እርሷንና ተከታዮቿን በጥሩ መስተንግዶ ተቀበላቸው፡፡ ንግሥት ሳባም የቤተ መንግሥቱን ሥርዓትና ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበቡን ቀሰመች፡፡ በኢየሩሳሌም ቆይታዋ ከንጉሡ ቀዳማዊ ምኒልክን ፀነሰች፡፡ ወደ ኢትዮጵያም ተመልሳ ልጇን ምኒልክን በዛሬዋ አሥመራ ከተማ አጠገብ እንደወለደችው ይነገራል፡፡
ይቆየን - ቀጣዩን በሚቀጥለው ክፍል
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቢ
-      መጽሐፍ ቅዱስ
-      ሐመር መጽሔት
-      ነቅዓ ጥበብ ዘፈለገ ሕይወት
-      የአክሱም ታሪክ






 ክፍል - ሁለት


የቀዳማዊ ምኒልክ ጉዞና የታቦተ ጽዮን መምጣት
ቀዳማዊ ምኒልክ ከአደገ በኋላ በ12 ዓመቱ ከእናቱ የተሰጠውን ለታቦተ ጽዮንና ለንጉሥ ሰሎሞን እጅ መንሻ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ ንግሥት ሳባም ለንጉሥ ሰሎሞን “ንጉሥ ሆይ ልጄን ሙሴ የጻፋቸውን ሕግጋት ሥርዓተ ክህነት አስተምረህ ላክልኝ፡፡” የሚል መልእክት ልካ ነበር፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ በኢየሩሳሌም ከአባቱ ዘንድ ለሦስት ዓመት ያህል ቆይቷል፡፡  በዚሁ ዘመን መጻሕፍተ ሙሴን፣ ሕገ መንግሥትን፣ ሥርዓተ ክህነትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ከሊቀ ካህናቱ ከሳዶቅ ተምሯል፡፡
 ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም በፈቃደ እግዚአብሔር ታቦተ ጽዮንን ይዞልን መጥቷል፡፡ ይህች ታቦት ለ3000 ዓመታት ያህል እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ በአክሱም ትገኛለች፡፡ ንግሥት ሳባም ታቦተ ጽዮን መምጣቷን ስትሰማ ለእግዚአብሔር መስዋዕት አቀረበች፡፡ ሰዎችን መርጣ ታቦተ ጽዮንን እንዲጠብቁ አድርጋለች፡፡ የመንግሥቱን ሥልጣን በሙሉ ለቀዳማዊ ምኒልክ አስረክባ ከዚህ ዓለም በሞተ በተለየች ጊዜ በዚያው በአክሱም ተቀብራለች፡፡ ቦታውም እስከ አሁን ድረስ የንግሥት ሳባ መቃብር እየተባለ ይጠራል፡፡
በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ታሪክ ጸሐፊው አቡሳላህ “አቢሲኒያውያን በእግዚአብሔር ጣቶች አሥርቱ ቃለት የተጻፈባት፣ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ያሉባት የቃል ኪዳኑ ታቦት አለቻቸው፡፡” በማለት ጽፎ ነበር፡፡ በዘመናችን ይህችን ታቦት ፍለጋ ያደረገው ግርሃም ሐንኮክም   “The sign and the seal” በተሰኘው መጽሐፉ ይህን ገልጦታል፡፡
ታቦተ ጽዮን በአክሱም


በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ሥፍራ ከያዙት ቦታዎች ግንባር ቀደምትዋ የአክሱም ከተማ ናት፡፡ አክሱም የኢትዮጵያ የታሪክና የሃይማኖት እናት ከተማ ስትሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ሺ ዓ.ዓ. እንደተቆረቆረች መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ አክሱም የቤተ ክህነቱም ሆነ የቤተ መንግሥቱ ማዕከል በመሆን ለብዙ ዘመናት አገልግላለች፡፡ በተለይም እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያተ ሙሴ የሰጠው የታቦተ ጽዮን  መንበር በመሆኗ ከተማዋን ድንቅ ሁኔታን ያጎናጽፋታል፡፡
በዘመነ ሐዲስም የክርስትና መዲና፣ የስብከተ ወንጌል ማዕከል ፤ የጳጳሳት መንበር ለመሆን መቻልዋም በቤተ ክርስቲያናችን የታሪክ ክፍል ውስጥ እንደ አጥቢያ ኮከብ እንድታበራ አድርጎአታል፡፡ የአክሱም ከተማ የ4000 ዓመት ዕድሜ ያላት ሲሆን ስለ ስያሜዋም ሊቃውንቱ ሲያትቱ፡-
1.       ከጌታችን ልደት በፊት 2000 ዓመት ገደማ የነበረውና የኩሽ የልጅ ልጅ /የኖኅ የልጅ፣ልጅ/የሆነው አክሱማዊ ስሙን ለቆረቆሩት ከተማ ማውረሱ ይነገራል፡፡ ከተማውን በቆረቋሪው መሰየም የጥንት ሰዎች ባህል ነበር፡፡ ዘፍ. 10፡1-32
2.      “አክሱም” የሚለው ቃል ከሁለት ጥንታውያን ቋንቋዎች የተገኘ ነው፡፡ “አኩ” በአገውኛ ቋንቋ ውኃ ማለት ሲሆን “ሱም” ደግም ከሴም ቋንቋ ተወስዶአል፡፡ ትርጉሙም “ሹም” ማለት ነው፡፡
3.      በሰሜን አክሱም አንድ የውኃ ጉድጓድ አለ፡፡ እሱም “ማይሹም” ይባላል፡፡ የከተማዋ መጠሪያ ከዚህ የተወሰደ ሳይሆን እንዳልቀረ አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
4.      የአክሱም /አኩሽም - በዕብራይስጥ/ - ጥንታዊት፣ ቀዳማዊት የነገደ ኩሽ መዲና፣ አህጉረ ኩሽ ማለት ነው፡፡
5.      ገድለ መርቆሬዎስ ደግሞ “መካነ ዕንቁ ማለት ነው” ይላል፡፡ ለዚህም “ወበእንተዝ ተሰምየ ስማ ለይእቲ አክሱም፣ እስመ ትርጓሜሃ ለአክሱም መካነ ስም ብሂል ዝውእቱ መካነ ዕንቁ፡፡”  እንዲል፡፡
የአክሱም ከተማ ታሪክ ይበልጥ እየገነነ የመጣው ከጌታችን  ልደት በፊት 1000 ዓመተ ገደማ ጀምሮ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ዘመን ንግሥት ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘችበትና ልጇ ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን በጥበበ እግዚአብሔር ወደ ኢትዮጵያ ያመጣበት ዘመን በመሆኑ ነው፡፡
የጽዮን በዓል አከባበር

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ኅዳር 21 ቀን  በታላቅ ክብር ታከብረዋለች፡፡ በዚሁ ዕለት የእመቤታችን ወዳጆች ምእመናን በዓሉን ለማክበርና ለመሳለም ወደ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በብዛት ይገሠግሳሉ፡፡ ዕጣን፡ ጧፍ፡ ዘቢብ መባውን ይሰጣሉ፡፡ ካህናቱም ከዋዜማው ጀምረው በከበሮና በጸናጽል ስብሐተ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፡፡ በድርሳነ ጽዮን መጽሐፍ ካህናቱ እንደተገለጠው በጽዮን ፊት እንደየመዓርጋቸው ቆመው  “እግትዋ ለጽዮን ወህቅፍዋ” የሚለውን መዝሙር ከዳዊት እያወጣጡ ይጸልያሉ፡ ይዘምራሉ፡፡ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ የታቦተ ጽዮንን ተራዳኢነት በምእመናን ፊት ይመሰክራሉ፡፡
 
ነቢያት ክርስቶስ ወዲዚህ ዓለም በሥጋ ማርያም ከመገለጡ በፊት ከእግዚአብሔር ተልከው ሕዝቡን ከአምልኮተ ጣዖት ከገቢረ ኃጢአት እንዲጠበቅ የሚመክሩ የሚያስተምሩና የሚያጽናኑ ነበሩ፡፡ ሉቃ 16፤17፣ ኢሳ. 40፤1፣ ኢሳ. 44፤1-11፡፡ የነቢያት ትንቢት ዋናው ዓላማ እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡን እንደተዋቸው እንደማይቀር፣ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰው ሆኖ ተገልጦ ወንጌልን አስተምሮ ስለእኛ መከራን ተቀብሎ እንደሚያድነን መግለጥ ነበር፡፡ ኢሳ. 7፤14፣ ማቴ. 1፤ 23፣ ሚክ. 5፤2፡፡
ነቢያት ሁሉ ስለ ክርስቶስ በተለያየ ኅብረት ትንቢትና አምሳል እንደ ተናገሩ ሁሉ ክርስቶስ ስለሚገኝባት አማናዊት ድንግል ማርያምም ተናግረዋል፡፡ ስለ ክርስቶስ በትንቢትና በተምሳሌት የተናገሩ ሁሉ ስለርሷ ተናግረዋል፡፡

ኅዳር 21 ቀን የሚከበረውም የእመቤታችን ምሳሌዎች የተገለጡበት እና የተለያዩ ሥራዎች የተሰሩበት ዕለት ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህም፡-
1.     ነቢዩ ዘካርያስ ሁለንተናው ወርቅ የሆነ፣ የዘይት ማሰሮ በራሱ ላይ የነበረበትንና ሰባት መብራቶች ያሉትን መቅረዝ ሲያበራ ያየበት ዕለት ነው፡፡ ዘካ. 4፤1-2፡፡ ዘካርያስ ያየው ብርሃን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ. 8፤12፡፡ ይህ ብርሃን የታየባትና የተገለጠባት መቅረዝ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ ብርሃን መቅረዝ እንዲያዝና እንዲገለጥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ተገልጦልናል፡፡ ጨለማ ዓለምን አብርቷል፡፡ ብርሃን ክርስቶስን ወልዳለችና እርሷም እመ ብርሃን / የብርሃን እናት/ ትባላለች፡፡
2.     ታቦተ ጽዮን ዳጎንን ገልብጣ በመጣል ኃይሏን የገለጠችበት ዕለት ነው፡፡ በፍልስጥኤማውያን ተማርካ ቤተ ጣዖት ወስደው ከጣዖታቸው ከዳጎን በታች አስቀምጠዋት ነበር፡፡ ታቦተ ጽዮን ግን በላይዋ ያለውን ዳጎንን ገልብጣ ጥላ እርሷ ከላይ ተቀመጠች፡፡ በታቦት የሚገለጠው የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ ምክንያቱም በታቦቱ ላይ ያለው ሕገ እግዚአብሔርና ስመ እግዚአብሔር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስም የጸና ክንድ ነውና ሁሉን ያሸንፋል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ለጊዜው ስትማረክ ደካማ ብትመስልም መማረኳ  ግን ኃይሏን ለመግለጥ፣ ለአሕዛብ የጣዖትን ከንቱነት የታቦትን ክቡርነት ለመግለጥ ነበር፡፡ 
3.    ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦቱን ይዞ አክሱም የገባበት፣ ንግሥት ሳባ ታላቅ በዓል አድርጋ የተቀበለችበት፣
4.    አብረሃ ወአጽብሐ በአክሱም ከተማ 12 ቤተ መቅደስ ያለው ቤተ ክርስቲያን በአስደናቂ ሁኔታ ሠርተው ከጨረሱ በኋላ ቅዳሴ ቤቱን ያከበሩበት፣ እንዲሁም
5.    በ9ኛው መ/ክ/ዘመን ዮዲት ክርስትና ለማጥፋት በተነሳች ጊዜ በእርሷ ምክንያት ታቦተ ጽዮን ወደ ዝዋይ ሐይቅ የተሰደደችበት፡፡ በኋላም የሰላሙ ዘመን ሲመጣ ተመልሳ አክሱም የገባችበት በዚሁ በኅዳር 21 ስለሆነ በእነዚህ በተደራራቢ ታሪኮች ምክንያት በየዓመቱ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል “ኅዳር ጽዮን በአክሱም ጽዮን” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

ታቦተ  ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡

ሀ.    ታቦተ ጽዮን በወርቅ የተለበጠች ናት፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስ በሥጋዋ ንጽሕት የመሆንዋ ምሳሌ ነው፡፡ ወርቅ የንጽሕና የቅድስና ምሳሌ ነው፡፡ ሰብአ ሰገል ካመጡት እጅ መንሻ አንዱ ወርቅ ነው፡፡ ይኸውም የክርስቶስ ንጹሐ ባሕርይነት የሚገልጥ ነው፡፡
ለ.      እስራኤላውያን በምድረ በዳ 40  ዓመት መና መግቧቸዋልና ይህን ለሚመጣ ትውልድ በታቦቱ ዘንድ እነዲያስቀምጡ ታዘው ነበር፡፡ አንድ ጎሞር መና በታቦቱ ፊት አሮን አስቀመጠ፡፡ ዘጸ. 16፤31-34፡፡ እስራኤላውያን የተመገቡት መና የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ. 6፤58፡፡ መናው የተቀመጠበት ጽላተ ኪዳን ደግሞ አማናዊ መና ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡
ሐ.     በጽላቱ ላይ በእግዚአብሔር ጣት 10ቱ ቃላት ተጽፈዋል፡፡ ጽላቱ የእምቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጽላቱ ላይ የተጻፈው ቃሉ የሥግው ቃል የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐንስ በመጀመሪያ ቃል ነበር፡፡ ዮሐ. 1፤1 እንዳለ፡፡ በጽላቱ ላይ በአጻብአ እግዚአብሔር የተጻፈው ቃል ቃለ እግዚአብሔር ከእመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ሕዋሳቶቿን ሕዋሳቱ አካሏን አካሉ አድርጎ ሰው የመሆኑ ምሳሌ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ታቦተ ጽዮን ዳጎንን መቀጥቀጧና በክብር መመለሷ እመቤታችንም በእናቷ በሐና ማኅፀን ሳለች ጀምሮ የተነሱባትን  ጠላቶቿን አይሁድ አጋንንትን በኃይለ እግዚአብሔር ድል አድርጋ የአምላክ እናት ለመሆን ለመብቃቷና ከርሷ የሚገኘው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጋንንትን ድል አድርጎ ግእዛነን እንደሚመልስልን፣ ከሲዖል ነፃ እንደሚያወጣንና በክብር ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ጥንት አኗኗሩ እንደሚያደርግ የገለጠና ያስረዳ ተምሳሌት ነበር፡፡
ታቦተ ጽዮን በእግዚአብሔር ፈቃድ በቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ኢትዮጵያ ገብታ በአክሱም ከተቀመጠችበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራችን በረከት፣ ረድኤት ሳይለያት በየዘመኑ የተነሱ ጠላቶችን ድል እያደረገች መልሳለች፡፡ እግዚአብሔር በታቦተ ጽዮን ላይ በረድኤት እያደረ የሕዝቡን ችግር እንዳስወገደ ሁሉ ዛሬም ችግራችንን እንዲያቃልልን፣ በረድኤት እንዲጎበኘን ዘወትር በጸሎት ታቦተ ጽዮንን ልንማጸን ይገባል፡፡ ለእስራኤላውያን በታቦቱ ላይ እያደረ እየተገለጠ ያናገረ የባረከ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

ጽዮን የተባለች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጣዕመ ውዳሴዋ ሀብተ ረድኤቷ በሁላችን ላይ አድሮብን ይኑር፡፡ 
ለዘላለሙ አሜን፡፡
በዓሉን በዓለ ፍስሐ በዓለ ደስታ ያድርግልን

No comments:

Post a Comment