Saturday 21 July 2012

ቤተክርስቲያን እንዴት ተመሠረተች ?

ዲያቆን መልአኩ እዘዘው








ስለ ክርስትና ሃይማኖት ስለ ቤተክርስቲያን በምንናገርበት ጊዜ ሁሉ ትዝ የሚለንና የምናስተውለው የመጀመሪያው ሰው የአዳም ሁኔታ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚአብሔር የሁላችንን አባት አዳምን በአርአያውና በመልኩ ከፈጠረው በኋላ ባረከው፡፡
ኹሉንም እንዲገዛ ሥልጣን ሰጠው፡፡ በረከቱን ሥልጣኑንና ሲሳዩን ከሰጠው በኋላ ፈጣሪውን የሚያስታውስበት ትእዛዝ አዘዘው፡፡ እሱ ግን በተሳሳተ ምክር ተመርቶ ከፈጣሪው ትእዛዝ ወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ ይህም የሞት ቅጣት ለርሱ ዐቅም ቀላል አልነበረም፡፡ በሱም ብቻ አልቀረም የልጅ ልጆቹ ይህን የሞት ቅጣት በውርስ ተካፈሉት፡፡ የዚህ የሞት ጽዋ ተካፋዮች ሆኑ፡፡ የአዳም ሕግን መተላለፍ የልጆቹም ተባባሪነት በእግዚአብሔርና በነሱ መካከል ያለውን ልዩነት እያሰፋው ሔደ፡፡ የፈጠራቸው እግዚአብሔርን ዘንግተው የሰማይና የምድርን ሠራዊት ማምለክ ጀመሩ፡፡ በጨረቃ፣ በፀሐይና በከዋክብት፣ በእሳት፣ በውኃ፣ በእንስሳትና በአራዊት፣ በዛፍና በተራራ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰውን ዘር ጨርሶ ለመደምሰስ ስላልፈለገ ይህን የሰው ልጅ መራራና አሰቃቂ ታሪክ ከመጀመሪያው ጀምረው ሲከታተሉ የነበሩ በአንድ አምላክ በማመን የታወቁ ጥቂት ሰዎችን አተረፈ፡፡ እነሱም ከአበው ሄኖክን፣ ኖህን፣ አብርሃምንና ሎጥን ሌሎችንም የመሳሰሉትን ነው፡፡ ከአብርሃም ይስሐቅ፣ ከይስሐቅ ያዕቆብ ተወለደ፡፡ ከያዕቆብም አሥራ ሁለት ልጆች ተወለዱ፡፡ አሥራ ኹለቱን የእሥራኤል ነገድ መሠረቱ፡፡

ለነሱም አንዳንድ ጊዜ ራሱ እግዚአብሔር እየተገለጠ አንዳንድ ጊዜም በነቢያትና በካህናት አማካይነት ሕጉንና ትእዛዙን ይሰጣቸው ነበር፡፡ መላልሶ ተአምራት ያደርግላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በአካባቢያቸው በነበረው የአረማውያን ተጽዕኖ ምክንያት እነዚህ ሰዎች አልፎ አልፎ በየጊዜው ወደ አምልኮ ባዕድ ይወድቁ ነበር፡፡ በአንድ ወገን ይህ ሲሆን በሌላው ወገን ሲታይ ደግሞ ከእውነተኛው የአንድ አምላክ እምነት ያላፈነገጡ፤ በአምልኮ ባዕድ ያልተለወጡ ብዙ እሥራኤላውያን ነበሩ፡፡ እነዚህ አምልኮታቸው የጸና ነበር የሚባሉት እሥራኤላውያን ከኃጢአት ለመንጻትና የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ ለመጠየቅ ብዙ ወይፈኖችንና ጊደሮችን ይሠዉ ነበር፡፡ እግዚብሔርን ደስ ቢለው በማለት በወርቅ የተለበጠ በሐር የተጨመጨመ ቤተ መቅደስ በሰሎሞን ተሠርቶ ነበር፡፡
እግዚአብሔር በነቢያት እያደረ የሚመልሰው መልስ ይህን ሁሉ ደስ ብሎት የተቀበለው አለመሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ የሰው ልጅ የታሪክ ጉዞ በኋላ እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ የሰውን ልጅ ለማዳን የቀጠረው ቀን ሲደርስ ልጁን ሰው ይሆን ዘንድ ላከው፡፡ በልጁ በክርስቶስ ሞት ቤተክርስቲያን ተመሠረተች፡፡
ቤተክርስቲያን የተወለደችው ወይም የተመሠረተችው በፍልስጥዔም ምድር ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከላይ እንደተገለጠው የሰውን ልጅ ትክክለኛ ታሪክና ሃይማኖት የያዙ የእግዚአብሔርንም የምሕረት ቀን በተስፋ ሲጠባበቁ የነበሩ በትዕግሥታቸው የተመሰገኑ ብዙ ደጋግና ቅዱሳን ሰዎች ስለነበሩባት ነው፡፡ የእግዚአብሔርንም የማዳን ሥራው ድንገተኛ ሳይሆን ለብዙ ዘመናት በተስፋ ሲጠበቅ የቆየ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት የታሪክ ሃይማኖት ነው መባሉም በዚህ ነው፡፡
 ክርስትና በተወለደበት ጊዜ የነበረውን የፍልስጥኤም ሁኔታ ለማጤን የሚቻለው ቀደም ካለው ሁኔታ የጀመርን እንደሆነ ነው፡፡ ፍልስጥዔም የአብርሃም የቃልኪዳን አገር ከነዐን ናት፡፡ በሌላም አነጋገር ምድረ ርስት ትባላለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የያዕቆብ ልጆች በሙሉ ከዚች አገር ተሰደው በግብጽ በባርነት ይኖሩ ነበር፡፡ ዘመኑም 17ዐዐ-13ዐዐ ከጌታ ልደት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ከጌታ ልደት በፊት 13ዐዐ ዓመት ገደማ በሙሴ መሪነት ወደዚች አገር ተመልሰዋል፡፡ በ1922 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት አሥራ ኹለቱ ነገድ ባገዛዝ ተጣልተው ለሁለት ተከፈሉ፡፡ አሥሩ ነገድ በሰሜን ፍልስጥኤም በሰማርያ ተቀመጡ፡፡ ከተማቸው ሴኬም ነበረች፡፡ ኹለቱ ነገድ ደግሞ በደቡብ ፍልስጥኤም ሰፈሩ፡፡ ከተማቸውም ኢየሩሳሌም ነበረች፡፡
በ792 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት ሰሜኑን ክፍል እስራኤላውያን በስልምናሶር መሪነት መጥተው አጠፏት፡፡ ሕዝቡም ተማረኩ፡፡ ይህ ሲሆን በደቡብ ክፍል የነበሩት የተማረኩትን አሥሩን ነገድ እንደ ጠላት ይቆጥሯቸው ስለነበር ሳይደሰቱ አልቀሩም፡፡ ነገር ግን በ586 ከጌታ ልደት በፊት የሴኬም ፅዋ በኢየሩሳሌምም ደረሰ፡፡ በናቡከደነፆር መሪነት ባቢሎናውያን መጥተው ኢየሩሳሌምን አጠፉ ሕዝቡንም ማርከው ወሰዱ፡፡ ሰባ ዓመት በምርኮ ቆይተው ከተመለሱ በኋላ ጥቂት እንደቆዩ በፋርስ ተወረሩ፡፡ አሁንም እንደገና በ33ዐ ከጌታ ልደት በፊት ግሪኮች በዚች ምድር ላይ ቅኝ ገዢዎች ሆኑ፡፡ በመጨረሻም 63 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት ሮማውያን ተረከቧት፡፡ እንግዲህ በዚህ ረጅም የተፋልሶ ጊዜ ሕዝቡ ብዙ የባህልና የሃይማኖት ቀውስ ደርሶበታል፤ እስራኤላዊ ያልሆኑ ጠባዮችንም ሳያውቀው ሸምቷል፡፡ ክርስትና በፍልስጥኤም ሲመሠረት የነበረውን ሁኔታ ለማወቅ የሚቻለው ይህ ሲታይ ነው፡፡
ክርስትና ሲወለድ ምድረ ፍልስጥኤም እንደ ሌሎቹ የመካከለኛው ምሥራቅ የሰሜን አፍሪካና የታናሽ እሲያ አገሮች በሮም ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች፡፡ በውስጥም የነበሩ ሕዝቦችም የተከፋፈለ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድን ነበራቸው፡፡ ከነዚህም ዋናዎቹ የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ቡድኑች ነበሩ፡፡
የሰዱቃውያን ቡድን የሀብታሞችና የካህናት ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን ለባሕል፣ ለሥነ ሥርዓትና ለሃይማኖት ግድ የሌለው ከቅኝ ገዢዎች ጋር ተስማምቶ በነሱ ሥልጣኔ መጠቀምን ብቻ እንጂ የነቢያትን ትንቢትና ሌሎችንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አይቀበሉም ነበር፡፡ የሙታንን ትንሣኤና የመሲሕንም መምጣት አያምኑም ነበር፡፡
 ሌላው ቡድን የፈሪሳውያን ቡድን ነው፡፡ ፈሪሳዊ “ፖርሽ” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ነው፤ ትርጉሙም “የተለየ” ማለት ነው፡፡ እነዚህ ፈሪሳውያን ምንም የቅኝ አገዛዝ ቀንበር መላልሶ ቢያደቃቸውም ባህልና ልምዳችን አይነካ በሃይማኖትም የሙሴን ሕግና የነቢያትን መጻሕፍት የምንጠብቅ እኛ ብቻ ነን ባዮች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ከአይሁድ ዘር ውጭ ከሆነ ከማንኛውም ጎሳና ዘር ጋር በባህልና በሥልጣኔ መቀራረቡን እንደ መርከስና ሕግን እንደመተላለፍ ይቆጥሩ ነበር፡፡ የመሲሕንም መምጣት ነቅተውና ተግተው ይጠባበቁ ነበር፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያታቸው ሀገራቸው ፍልስጥኤምን ከሮም ግዛት ነጻ ለማውጣት የቆየ ጉጉት ስላላቸው ነው፡፡ እንደነሱ አስተሳሰብ መሲሕ ሲመጣ የጦር ኃይል አቋቁሞ ራሱ የጦር መሪ በመሆን የሮማን የቅኝ ግዛት ቀንበር አውልቆ ጥሎ የዳዊትን ቤተ መንግሥት የሚያድስ መሲሕ ይጠባበቁ ነበር ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ከትንሣኤ በኋላ ሥጋዊ ኑሮ አለ ብለው ቢያምኑም ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ያውቁ ነበር፡፡
ፈሪሳውያን በዕለታዊ ኑሮአቸው ብዙ ሀብት ፍልስጥኤምን ነጻ ያወጣል የሚለውን የፈሪሳውያን እምነትና ተስፋ በመቃወም ሌላ ንኡስ ቡድን ከፈሪሳውያን ተከፍለው በሙት ባሕር አካባቢ ገዳም መሥርተው ይኖሩ ነበር፡፡ የእነሱም ዓላማቸው እንደ ፈሪሳውያን መሲሕን መጠባበቅ ነው፡፡ ኤሤይ በመባል የታወቁት እነዚሁ ክፍሎች ከፈሪሳውያን የሚለዩት ፈሪሳውያን በጦር ኃይል ነጻ እንወጣለን ሲሉ ኤሤይ የሚባሉት ደግሞ በተአምራት በእግዚአብሔር ኃይል ፍልስጥዔም ነፃ ትወጣለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ በቤተልሔም በስተደቡብ ልዩ ስሙ ኩምራን በሚባል ቦታ የሚኖሩ እነዚህ ሰዎች መጻሕፍትን በመጻፍ ጸሎትን በማድረስ ብዙ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ ኤሤዎችና ፈሪሳውያን ባንድ አንድ አስተሳሰብ ቢለያዩም መሲሕ መምጣቱንና የተወሰኑ ምርጥ ጎሳዎችን ነጻ እንደሚያወጣ ዓለም አቀፋዊ መሲሐዊ መንግሥት እንደሚያቋቁምና እነሱም የመንግሥት ባለሟሎች እንደሚሆኑ ሁለቱም ቡድኖች ያምኑ ነበር፡፡ በእስራኤል የሃይማኖትና የነገድ ቤተሰብ ውስጥ ይህ ልዩነት ተፈጥሮ መከራቸውን ሲያዩ በፍልስጥኤምና ከፍልስጥኤም ውጭ የነበረው የሮማ መንግሥት ፖለቲካ ደግሞ ከቅኝ ግዛቱ የተነሣ ያነገንግ ነበር፤ የነጻ አውጭ ግንባሮች በየጊዜው የሕዝብ ቆጠራ እንዲደረግ ታዞ ነበር፡፡
ሕዝቡ በጠቅላላ ገበሬውም ሆነ ነጋዴው የመንግሥትም ባለሥልጣን በሚሠራው ሥራ ሁሉ ባለጸጋ ስለነበር የሮም ግዛት ተወዳዳሪ የሌላት ታላቅ አገር ነበረች፤ ታዲያ ምን ያደርጋል እነዚህ ሁሉ ሀብታት ለሕዝቡ ደስታና ውስጣዊ ዕረፍትን ሊያገኙለት አልቻሉም፡፡ ሁልጊዜ በአካባቢው ከሚሰማው የሽብርና የሁከት ድምጽ የተነሳ ባልታሰበ ቀን እንደመስሳለን በሚል ቀቢጸተስፋ ገዝቶት ነበር፤ ያመልኳቸው ከነበሩ ጣዖታትም አንዳችም የተስፋ ድምጽ አልነበረም፡፡ በቀቢጸ ተስፋ ባሕር ውስጥ ገብቶ የሚማቅቀውና መውጣትም የተሳነው አማኛቸውን ሊያረጋጉት አልቻሉም፡፡
ዳዊት እንደተናገረው ዓይን እያላቸው የማያዩ፤ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፤ እጅ እያላቸው የማይዳስሱ አፍ እያላቸው የማይናገሩ፤ እግር እያላቸው የማይሄዱ ግዑዛን ናቸውና፡፡ ከዚህም የተነሣ ማለት የሚያመልኳቸው ጣዖታት ሊያረጋጓቸውና ሊረዷቸው ስላልቻሉ ሕዝቡ “አማልክቶቻችን የዋሃንና ግድ የለሾች ናቸው” እያሉ በጣዖታቱ ይዘብት ነበር፡፡ የሰው ልጅ ሥልጣኔም በክፋትና በደግነት መካከል የለውን ልዩነት ለማመልከት አልቻለም፡፡ በዚህም አኳኻን ስለ ሰው ልጅ የወደፊት ዕድል ምንም የተስፋ ጭላንጭል አልነበረም፡፡ ሰው በተፈጥሮው ከወዴት መጣሁ? ወዴትስ ነው የምሔደው? ብሎ ራሱን በራሱ የመጠየቅና የመመርመር ስጦታ ያለው ባለአእምሮ ፍጡር ስለሆነ እነዚህ ጥያቄዎች ሁልጊዜ በፊቱ ይደቀኑበታል፡፡ ነገርግን ለነዚህ ጥያቄዎች ከውስጥ ከራሱም ሆነ ከውጭ ከሌላ አጥጋቢ መልስ ስላላገኘ ከላይ እንደገለጥነው የደስታና የኑሮ ጣእሙንና ምሥጢሩን ሊያውቀው አልቻለም፡፡ በሮም ቅኝ ግዛት ውስጥ የሚኖር ሁሉ በዚህ ሁኔታ በቀቢጸ ተስፋ ስለተሞሉ እነሱም ሆነ ሥርዓተ ማኅበራቸው ጠባቂ እንደሌለው መርከብ አቅጣጫው የማይታወቅ ሆነ፡፡ ሕዝቡን ለማስደሰት በሮም የቴያትር ሰገነት ላይ የሚቀርበው የጨዋታ ዓይነትም እንኳ ደም መፍሰስና መደባደብ ስለነበር በጨለማ ላይ የዛፍና የገደል ጥላ ሲጨመር ጨለማው እንደሚጸና ሰቀቀኑን አባብሶት ነበር፡፡ 
ሀብታም በሀብቱ ደስታን ለመሸመት አልሆንለት ብሎ ሲጨነቅ ሲጠበብ በዝቅተኛው ሕዝብ ዘንድ ደግሞ ዕጓለማውታንና መበለታትን ወዴት ወደቃችሁ የሚላቸው አልነበረም፡፡ በሽተኞችና ረሀብተኞች ጥርኝ ጥሬ ኩባያ ውኃ የሚላቸው አጥተው በረሀብ ይተላለቁ ነበር፡፡ ሲሞቱም የአውሬ ራት እንጂ የሚቀብራቸው አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ፍርድ ጎደለ፣ ድሃ ተበደለ የሚል ታዛቢ ተመልካች የሌለበት የአስረሽ ምችውና የብላ ተበላ ዘመን ነበር፡፡ የሰው አውሬው ሰው ነው የሚባለው የሮማውያን ተረት የተፈጸመው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ እነ አውግስጦስ ቄሣር የሰላም እመቤት ብለው የሰየሟት ወይም ራሷን ሰላም ብለው የጠሯት ፖክስ ሮማና ፍቅርና ሰላምን አላስገኝላቸውምና ይህ ሁሉ ሁከትና የሽብር ጥላ ባንዣበበት ወራት የቤተክርስቲየን መሠረት የአሕዛብ ብርሃን የእሥራኤል ዘነፍስ ክብር መድኃኒዓለም በሮም ቅኝ ግዛት ሥር በነበረች በፍልስጥኤም ልዩ ስሟ ቤተልሔም በምትባል በይሁዳ ክፍል ተወለደ፡፡ በተወለደም ጊዜ ትንቢት ያልተነገረላቸው ሱባኤ ያልተቆጠረላቸው ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰብአ ሰገል መድኅን መወለዱን አውቀው ከምድረ አሕዛብ እጅ መንሻውን ወርቅ፣ ዕጣን ከርቤ ይዘውለት መጡ፡፡ ገበሩለትም፡፡
በመድኅን መወለድ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ መላእክትም ተደስተዋል፡፡ “በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል፤ በምድርም ሰላም” እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ባንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ደግሞ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ለምሳሌ ሥርዓተ ኦሪትን ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከታተላለን ይሉ የነበሩ ፈሪሳውያን ክንዱ የሚያደቅ ግርማው የሚያንቀጠቅጥ ሮማውያንን አባሮ አገራቸው ፍልስጥኤምን ነጻ የሚያወጣ ኃይለኛ መሲሕ ሲጠባበቁት ሁኖ አልመጣም እንዲያውም ከላይ እንደተገለጠው ዘመኑ የሁከትና የሽብር ዘመን ስለነበር አውግስጦስ ቄሣር ለጸጥታ አጠባበቅ እንዲያመች በየጊዜው ዜጎቹን ሲያስቆጥር ነበርና ድንግል ማርያም ለመመዝገብ ለመቆጠር አገር ጥላ ስንቋን ቋጥራ በሔደችበት ቦታ መጠጊያ እንኳ በሌለበት በተጨናነቀ አካባቢ ከብቶች በሚያድሩበት ቦታ መሲሕ ተወለደ፡፡ በዚያም የሀብታሞች የነገሥታት ልጆች ሲወለዱ በሚነጠፍላቸው ወርቀ ዘቦ ሳይሆን ሉቃስ እንደነገረን እናቱ በጨርቅ ጠቀለለችው፡፡ በዚህ ምክንያት ማለት እነሱ እንዳሰቡትና እንደተጠባበቁት ሆኖ ስላላገኙት ፈሪሳውያንም ሆኑ ሰዱቃውያን መሲሕነቱን አልተቀበሉትም፡፡ በተንኮል እየተመሣጠሩም በማስተማር ጊዜው ብዙ የንቀትና የተላልቆ ከቄሣርም ጋር የሚያጋጭ የፖለቲካ ጥያቄ ይጠይቁት ነበር፡፡
ፈረሳውያን ሙሴን እንወደዋለን ስለሚሉ በነቢያትም ተአምራት ስለሚኮሩ የሙሴንና የነቢያትን አምላክ “እንደ ሙሴ መና አውርዶ ደመና ጋርዶ እንደ ኤልያስ ዝናም አቁሞ እሳት አዝንሞ” እንዲያሳያቸው መላልሰው የፈተና ጥያቄ ጠየቁት እሱም ለጠየቁት ሁሉ በቃሉ ትምህርት በእጂ ተአምራት የሚገባ መልስ ሰጥቷል፡፡ በተለይም ሰዱቃውያን በምድር ብቻ እንጂ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ስለማያምኑ ስለ ትንሣኤ ሙታን የሚያደናግር ጥያቄ መስሎ የታያቸውን ጠየቁት፡፡ ለዚህም የማያዳግም መልስ ሰጥቷቸዋል፡፡ በፖለቲካም ከሮም መንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር ነገሩን ለማያያዝ ስለ ግብር አከፋፈል ማለት ለሮማ ቅኝ ገዥ ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም ሲሉ እነዚሁ ሰዱቃውያን የተንኮል ጥያቄ አቅርበውለት ነበር፡፡ ተንኮላቸውን ስለሚያውቅ፡ “የቄሳርን ለቄሣር መስጠት ይገባል፤ የእግዚብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው፡፡ መድኃኒታችን በዚህ በማስተማር ጊዜው የፈሪሳውያንም ኾነ የሰዱቃውያን ሁኔታ ግብዝነታቸውም ከልክ ያለፈ ስለነበር ለጥያቄያቸው መልስ ከመስጠት ጋር ይገሥጻቸው ነበር፡፡ እነሱም በበኩላቸው እሱን ለማጥፋት አድማ ይጎነጉኑበት ጀመር፡፡
የክርስቶስ መወለድና ትምህርቱም ያላስደሰታቸው የቤተ እሥራኤል ተመጻዳቂዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ የሮም መንግሥትም በበኩሉ ክርስቶስን በጥላቻ ዓይን ይመለከተው ነበር፡፡ የሮማ ቄሣር ወዳጅ በመሆኑ በገሊላ የነገሠ ሄሮድስ መሲሕ “ክርስቶስ” በቤተልሔም መወለዱን ከሰብአ ሰገል እንደሰማ የራሱንና መላዋንም የቄሣር ግዛት የሚቀናቀን ንጉሥ የተወለደ መስሎት ደነገጠ፡፡ የመሲሕ መወለድ ስላስደነገጠው ሕፃኑን መሲህ ለመግደል ሙከራ አደረገ፡፡ ነገርግን ሕፃኑ መሲህ የነቢያትን ትንቢት ለመፈጸም ከእናቱ ጋር ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡ የሄሮድስ ሰይፍ በአንገቱ ላይ አልወደቀችም፡፡ ነገር ግን በሄሮድስ ተንኮል ብዙ የገሊላ ሕፃናት በሰይፍ አለቁ፡፡ ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ የብዙ እናቶች እንባ በግፍ ፈሰሰ፡፡
ኋላም መሲሕ በማስተማር ጉዞው እንደ ፈሪሳውያንና እንደ ሰዱቃውያን የሄሮድስን ባለ ሥልጣኖችና ራሱንም ሄሮድስን በግብዝነቱ በይፋ ስለሚገሥጸው “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” እንደሚባለው በክርስቶስ ላይ ለማደም አመች ሆነ፡፡ ጌታ ግን የሮማ ቅኝ ገዥዎችና የቤተ እሥራኤል የኃይማኖት ሰዎች መሲሕነቱን ባያውቁለትም ለበቀል ሳይሆን ለምሕረት ለመዳን የመጣ እውነተኛ መሲህ እንደመሆኑ መጠን በነቢያት ስለ እሱ የተነገረውን ለመፈጸም ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ የማስተማር ሥራውን ቀጠለ፡፡ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የአመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጅ ለመሆን አበቃቸው፡፡ እነሱ ግን ጥላቻቸውን ወደ ግቡ ለማድረስ የተነሱና በሰይጣን የሚገፋፉ ስለሆኑ የርሱ ትሕትናና ፍቅር ቅንዓታቸውን አባባሰው እንጂ አልቀነሰውም፡፡ ስለዚህም በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን ከሳሽነት በሮማውያን ዳኝነት ክስ ተመሠረተበት፡፡ ክሱም ኃይማኖትንና ፖለቲካን የሚመለከቱ ጣምራ ነገሮችን የያዘ ነበር፡፡
የሮማ መንግሥት የዜጎችን እኩልነት ያከብራል እንዲባል በቅኝ ግዛት ውስጥ ለሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ የሃይማኖትና የባህል ነጻነት ሰጥቷቸው ነበር፤ አንዱ የሌላውን ሃይማኖት ቢነቅፍና ቢያዋርድ ወይም ከዚያም ከአንዱ ሃይማኖት ውስጥ አንዱ አዲስ ሐሳብ ቢጨምር ወይም ቢቀንስ ራሳቸው እንዲቀጡት ቅጣቱ በሕይወት ላይ የሆነ እንደሆነ ግን ወደ መንግሥት ባለ ሥልጣን አቅርበው እንዲያስፈርዱበት ሕግ ተሠርቶ ነበር፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም በክርስቶስ ላይ ክስ የመሠረቱበት ይህ መብታችን ተነክቷል፤ በቀላል ቅጣት የሚታለፍ ስላልሆነ በሞት ይቀጣልን ብለው ነው፡፡ “በፖለቲካ” መንፈስ የተመሠረተበት ሁለተኛ ክስ ደግሞ “እኛ ያለ ቄሣር ንጉሥ የለንም፡፡ እሱ ንጉሠ አይሁድ ነኝ እያለ ያስተምራል ሕዝቡ ለቄሣር እንዳይገብር ያሳድማል” የሚል ነበር፡፡ እንዲህ ማለታቸው በእውነት ፊሪሳውያንና ሰዱቃውየን ለሮማ መንግሥት አስበው አይደለም፡፡ የሮማ ባለሥልጣኖች ነገሩን ይዋል ይደር ሳይሉ እንዲያፋጥኑትና ጉዳዩ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የሮማንም የአገዛዝ አውታር የሚነቀንቅ ሰለሆነ መንግሥት ለራሱመ ጭምር ሲል ባስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድ ለዘዴ ነው፡፡ እነሱ ሰው ሰውኛውን ይህን ያህል ደከሙ እንጂ መሲሕ እንደሆነ በሃይማኖት የሙሴን ሕግ ይሽራል የሚለው ክስ ሳይመሠረትበት በፊት “የሙሴን ሕግ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም” እያለ ሲያስተምር እንደነበር በጆሮዋቸው ሰምተዋል፡፡
በማቴዎስ 09¸ 06-2 እድን ዘንድ ምን ላድርግ ብሎ ለጠየቀው ኦሪታዊ ባለጸጋ እንኳ የሙሴን ትእዛዝ እንዲጠብቅ አዘዘው፡፡ ፍጹም እንዲሆን ቢፈልግ ርግጥ በትሩፋት ላይ ትሩፋት ለመጨመር ቢፈልግ ሀብቱን ለነዳያን ሰጥቶ እሱን ቢከተለ የሚሻለው መሆኑን አልሰወረም፡፡ እነሱ የሚጠቅሱትን ሙሴም ስለርሱ የጻፈ ስለርሱ የተነበየ መሆኑን ነግሯቸዋል፡፡ በፖለቲካም ለቄሣር ግብር አትስጡ ብሎ ሕዝቡን ያሳምጻል ተብሎ ከመከሰሱ በፊት “ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባል ወይስ አይገባም?" ብለው በተንኮል ቢጠይቁት “የመንግሥታችሁን ለመንግሥታችሁ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” ብሏቸዋል፡፡
 እንደተገለጠው ለሮማ መንግሥት ግብር የሚሰበስቡ የመንግሥት ተወካዬች በጴጥሮስ በኩል ስለግብር ጉዳይ አንድ ጥያቄ አንሥተው ነበር፡፡ ጥያቄውም “መምህራችሁ ግብር ይከፍላልን” የሚል ነበር፡፡ ጌታም ይህን ጥያቄ ሰምቶ ምንም እንኳ አስገባሪ እንጂ ገባሪ አለመሆኑን ባይደብቃቸውም የነሱን የተንኮል ጥያቄ ባጭሩ ለመቅጨት ወዲያው ከባሕር ዓሣን ከዓሣ የወርቅ እንክብል አስገብሮ እንዲሰጣቸው ተማሪው ጴጥሮስን አዞታል፡፡ 

በዚያም ሆነ በዚህ ለጥላቻ ማጉሊያ ብለው እንጂ የጠበቁትማ ለቄሣር ግብር እንዳይሰጥ የሚከለክለውን የፖለቲካ መሲሕ አልነበረምን በመሲሕ ላይ ይሙት በቃ የሚያሰኝ ኃጢአት አልተገኘበትም፡፡ ሞቱ የሥርየት እንጂ የቅጣት ሞት አይደለምና በመጀመሪያ በአይሁድ ሊቃነ ካህናት ጉባኤ በኋላም ሮማ መንግሥት ተወካይ በጲላጦስ አደባባይ በዋለው ችሎት ይሙት በቃ ተፈረደበት፡፡ ሞቱም በመስቀል ላይ ነበር፡፡ በመስቀል ላይ እንዳለው በግፍ የሰቀሉትን ሰዎች ተቆጥቶ ማጥፋት ፈንታ “አባ ሥረይ ሎሙ እስመ ኢየአምሩ ዘይገብሩ፤ አባቴ ይቅር በላቸው የሚሠሩትን አያውቁምና” ብሎ ያች ሰዓት የምሕረትና የይቅርታ ሰዓት መሆኗን ነገረን፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ሰውን የቱን ያህል እንደሚወድና እንደሚታገሰው ያሳያል፡፡ ጌታ ይህን የምሕረት ቃል በተናገረ ጊዜ አዳም ከበደለ ጀምሮ የሰው ልጆች እንዳይገቡበት ተዘግቶ የነበረው የገነት በር ተከፈተ፡፡ በሰይጣን ቁራኝነት ተግዘው ለነበሩ ነፍሳትም በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ግዕዛነ ነፍስን ሰበከላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የምእመናን አንድነት መሠረት ተጣለ፡፡ ይህችውም ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ ሦስት መዐልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ሲፀነስና ሲወለድም የእናቱን ማሕተመ ድንግልና አልለወጠምና፡፡ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አበሰረን፤ ለትንሣኤያችን በኩር ሆነ፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ከፍ ብሎ በአራት ቀን ዝቅ ብሎ በሁለት ቀን ያልሆነበት በሦስት ቀን የሆነበት ምክንያት አለው፡፡ ይኸውም ዕብራውያን አንድ ሰው ፍጹም መሞቱን የሚረዱት በሞተ በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ በመቃብር የቆየው ሦስት መዐልት ሦስት ሌሊት ጌታ የተቀበረው ዐርብ ከአሥራ አንድ ሰዓት ከሰዓት በኋላ ድረስ ያለው የቅዳሜ መዐልትና ሌሊት ነው፡፡ ቅዳሜ ከአሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ያለው እሑድ ነው፡፡ አንዱም ሰዓት ቢሆን ከላይ እንደተገለጠው የዕለቱን ሰዓቶች ያሟላል፡፡ ጌታም የተነሣው እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ስለሆነ ሦስት መዐልት ሦስት ሌሊት ማለት ይህ ነው፡፡ 
ከተነሣም በኋላ ለደቀመዛሙርቱ አንዳንድ ጊዜ እየተገለጠ ሲታያቸው አርባ ቀን ያህል ቆየ፡፡ በትንሣኤው ስለተገኘው ድል የማበረታቻ ትምህርትን አስተምሯቸዋል፤ በንፍሐት ሥልጣነ ክህነት ሹሟቸዋል፡፡ በተነሣ በአርባ ቀኑ ወደ ሰማይ አረገ፤ በዚህም ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እልክላችኋለሁ፤ እስከዚያው ግን ከኢየሩሳሌም እንዳትወጡ ብሎ ትእዛዙን አዟቸው ተስፋውን ነግሯቸው አረገ፡፡ ባረገ በአሥረኛው በተነሣ በሃምሳኛው ቀን በገባላቸው ቃልኪዳን መሠረት በአንድ ላይ ተሰብስበው እንዳሉ መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው፡፡ ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ከብልየት ታደሱ በአእምሮ ጎለመሱ፡፡ ፍሩሓን የነበሩ ጥቡዓን ሁነው ፈርተው የካዱትና እየተንቀጠቀጡ ጥለውት የሸሹትን የክርስቶስን መስቀል ለመሸከም የማያወላውሉ ሆኑ፡፡ ትንሣኤውንም ለመመስከር በየአደባባዩ መሯሯጥ ሆነ፡፡ የአይሁድ ቁጣና ተግሣጽ አልመለሳቸውም፡፡ እንዲያውም ተገፈው ተገርፈው ሲመለሱ የንጉሥ ማለፊያ ቀምሶ እንደወ ባለሟል ደስ ይላቸው ነበር፡፡
የእግዚአብሔር ጥሪ ለመልካም አድራጊዎች ብቻ ሳይሆን ክፉ አድራጊዎችም ከክፋታቸው በንሰሐ ቢመለሱና በክርስቶስ ቢያምኑ ለማዳን ጊዜው ያላለፈ መሆኑንም ጠንክረው አወጁ፡፡ ይህም የቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ይህን ኹሉ ጥብዓትና እምነት ያገኙት አጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ስለሆነ የኋላ ሊቃውንት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉባትን ዕለት“የቤተክርስቲያን የልደት ቀን” ናት ብለዋታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ባይታደሱ ለክርስቶስ ትንሣኤ ምስክር ለመሆን ባልበቁም ነበር፡፡ “የቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት” ብለዋታል ሁሉንም የሚያነጻ ሁሉንም የሚቀድስ መንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን የተሰጠበት ቀን ነበርና፤ በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን የጀመረችው መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ 
የቤተክርስቲያን መመሥረት ያስፈለገበት ምክንያት በቅዱሳት መጻሕፍትና በአበው ትውፊት አማካይነት በአጭሩ ከዚህ በላይ ተዘርዝሮ እንደተገለጠው ነው፡፡

Wabi :የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
ብጹእ አቡነ ጎርጎርዮስ
አዲስ አበባ 1978

No comments:

Post a Comment