Saturday 25 February 2012

የዐብይ ጾም ስብከት (ክፍል 2) በአያሌው ዘኢየሱስ


የዐብይ ጾም ስብከት (ክፍል 2)

የካቲት 15/2004 ዓ.ም.
በአያሌው ዘኢየሱስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤አሜን፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጾም በድንገት የተገኘ የሰዎች ፍልስፍና ሳይሆን አምላካዊ ሥርዓት ነው፡፡ ጾም መጾም የተጀመረበት ጊዜ ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጋር የማይተናነስ መሆኑን የምናውቀው እግዚአብሔር አምላክ የቀደሙ ወላጆቻችንን፡- ከዚህ ብሉ፤ ከዚህ ግን አትብሉ (ዘፍ 2፥16-17) በማለት ከደነገገላቸው ትእዛዝ ጋር የሚዛመድ በመሆኑ ነው፡፡ «አትብሉ» ማለት ከተወሰነ ወይም ከተወሰኑ መባልእት «ተከልከሉ» አልፎ ተርፎም «አትንኩት» ማለት ነው፡፡ ዲያብሎስ እናታችን ሔዋንን «በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዟአልን?» (ዘፍ 3፥1) በማለት በጠየቃት ጊዜ እግዚአብሔር ለእርሷና ለባሏ የሰጣቸውን ቀጥተኛ ትእዛዝ ግልጽ በሆነ መንገድ የነገረችው እንዲህ በማለት ነበር፡- «እግዚአብሔር አለ፡- እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፤አትንኩትም፡፡» ዘፍ 3፥3፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የአዳምንና የሔዋንን ሕልውና ወይም መኖርና አለመኖርን የወሰነው በመብላትና ባለመብላት ውስጥ ነበር፡፡ አዳምና ሔዋን መብላትን ችለው አለመብላትን ስላልቻሉ ነው ከገነት ተባርረው የሞት ሞት  የተፈረደባቸው፡፡


ኦርቶዶክሳዊት የሆነችው የኢትዮጵያ የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ስለ ጾም መናገር ወይም ማስተማር የምትጀምረው ከዚህ ነጥብ ላይ በመነሣት ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ከተሳሳቱ በኋላ ጾመውና ንስሓ ገብተው ሲያለቅሱ እግዚአብሔር ከልጅ ልጃቸው ተወልዶ እንደሚያድናቸው ቃል ስለ ገባላቸው ከ5500 ዓመታት በኋላ ወደዚህ ዓለም በመምጣት ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ፤ ከደሟም ደም ነሥቶ በመወለድ፣ በመጠመቅ፣ በማስተማር፣ መከራ በመቀበል፣ በመሞት፣ በመነሣት፣ በማረግ እና ወደ ቀደመ ክብሩ በመመለስ አድኗቸዋል፤አድኖናል፡፡


ይህ ሁሉ ከመፈጸሙ በፊት ግን ነቢያትና ቅዱሳን አባቶች «ፈኑ እዴከ እም አርያም. . .»  «እጅህን (ልጅህን) ከሰማይ ላክ» በማለት በጾምና በጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔር ይጮሁ ነበር፡፡ ወላጆቻቸው /አዳምና ሔዋን/ አትብሉ ተብለው በመብላታቸው የሞት ሞት መሞታቸውንና ለመብል ማድላትም እንደሚጎዳ ያውቃሉና፣ ጾምን የመንፈሳዊ ሥራቸው አጋር በማድረግ ተጠቅመውበት አልፈዋል፡፡ በመሆኑም እገሌ ከእገሌ ወይም ይኼኛው ከተማ ከዚያኛው ከተማ ሳይባል በብሉይ ኪዳን ዘመን የኖሩ የእግዚአብሔር ሰዎች በሙሉ ጾመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡- ነቢዩ ዳዊት፣ መዝ 34፥13፣ 68፥10፣ 108፥24፣ ነቢዩ ዳንኤልና ነቢዩ ሕዝቅኤል፣ ዳን 3፥9፣ ሕዝ 4፥9፣ ነህምያና ሕዝቡ፣ ነህ 1፥3፣ 8፥21፣ የነነዌ ሰዎች፣ ዮና.3፥7-10፡፡


አስቀድመን እንደ ተመለከትነው እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት ጾምን የሕልውና ማለትም የመኖርና ያለ መኖር ወሳኝ ነጥብ እንዳደረገው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም «ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም፡፡» (ማቴ 4፡4) በማለት ሰውን በሕይወት የሚያቆየው መብላት ብቻ አለመሆኑን ገልጦልናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የአገልግሎቱን መጀመሪያ ያደረገው ጾምን ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሊፈትነው የመጣው ዲያብሎስ ያቀረበለት ሦስቱ አርእስተ ኀጣውእን ድል ያደረጋቸው በጾም መሆኑን አሳይቶናል፡፡ ከእርሱ በኋላ ዓለምን በስብከታቸው ለማዳረስ ወገባቸውን በእውነት ታጥቀው የተነሡት ሐዋርያትም ለአገልግሎት ከመውጣታቸው በፊት ጾመዋል፡- ይህ ከመሆኑ በፊት ጌታ ከእርሱ ጋር ያሉት ሐዋርያት እርሱ ከእነርሱ ሲለይ መጾም እንደሚጀምሩ እንዲህ በማለት አስረግጦ ነግሮናል፡- «ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡» ማቴ 9፥15፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሙሽራ ኢየሱስ ክርስቶስ በዕርገቱ ከእነርሱ ሲለይ ለመጾማቸው ማረጋገጫ የሚሆነን ደግሞ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተጻፈልን ቃል ነው፡- «በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቷቸው፡፡» ሐዋ 13፥3፡፡


ቅዱሳን አባቶች፣ ነቢያት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሐዋርያትና ሕዝቡ የጾሙት ጾም የተለያዩ ዐበይት ጥቅሞች ቢኖሩትም ከእነዚህ ጥቅሞቹ መካከል አንዱ ርኩሳን መናፍስትንና ዲያብሎስን ለማሸነፍና ለማራቅ ዓይነተኛ የጽድቅ መሣሪያ መሆኑ ነው፡፡ ይህን የጽድቅ መሣሪያ ገንዘብ ለማድረግ ግን ለታይታ የሚያጋልጡ ተግባራትን መፈጸም ተገቢ ነገር አይደለም፡፡ ከእነዚህ የታይታ ሥራዎች መካከል አንዱ ደግሞ ለሌሎች ሰዎች በጾም ላይ እንዳሉ የሚያስታውቀው መጠውለግና ፊትን ማጥፋት ነው፡፡ ይህ ሊደረግ እንደማይገባ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አበክሮ ሲናገር እንዲህ ብሎናል፡- «ስትጦሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉ፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል» ማቴ 6፥16፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ከተናገረ በኋላ በዚያው በማስከተል እኛ እንዴት መጾም እንደሚገባን አስረግጦ ሲነግረን እንዲህ ብሏል፡- «አንተ ግን ስትጦም፡- በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህ በግልጥ ያስረክብሃልና፡፡» ማቴ 6፥17-18፡፡


በክርስትና እምነት ውስጥ በሰዎች ፊት ከመታየት ሊሸሸጉ የማይችሉና የሚችሉ የጽድቅ ሥራዎች እንዳሉ አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ አንድ የተዋሕዶ ክርስቲያን ፍቅሩን፣ ትሕትናውን፣ መልካም ጠባዩን. . . ወዘተ በሰዎች ፊት ሊሸሽግ አይችልም፡፡ በአንጻሩ ግን በግሉ የሚያከውናቸውን የጽድቅ ሥራዎች ማለትም መጾሙን፣ መጸለዩን እና ምጽዋት መስጠቱን መሸሸግ ይችላል፤ይገባዋልም፡፡ ይህን ሳያደርግ ቀርቶ ሲመጸውት መለከት የሚያስነፋ፣ ሲጸልይ በመንገድ ዳር እና በአደባባይ ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቆሞ ለሰዎች ዐይን የሚጸልይ፣ ሲጦምም ለሰዎች እንደ ጾመኛ ለመታየት ፊቱን የሚያጠፋ ከሆነ ምድራዊ እንጂ ሰማያዊ ዋጋ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ይህ ስለሆነ ነው ጌታ አማናዊ በሆነው ቃሉ «ዋጋቸውን ተቀብለዋል» በማለት የተናገራቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሚጾሙ ጊዜ መጠውለጋቸው በሰዎች ዘንድ ካልታወቀላቸው ለሚቀርቧቸው ሰዎች ስለ መጾማቸው በተለያየ መንገድ መናገር ይጀምራሉ፡፡


ሰዎች እንዲዚህ ዓይነቱን የታይታ ሥራ የሚሠሩት ለምንድር ነው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ በሰዎች ዘንድ ከበሬታንና ሙገሳን እንዲሁም ውዳሴን ለማግኘትና ለመቀበል ነው አለያም ከትምህርት ማነስ የሚል ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ከሌላ ሰው የሚያገኘው ወይም የሚቀበለው ከበሬታ ወይም ሙገሳ ወይም ውዳሴ ሊጠቅመው የሚችለው ነገር ምንድር ነው? ሰው እኮ ዛሬ ቢያወድስ ነገ ሊያኮስስ ወይም ሊያዋርድ ይችላል፡፡ ሰው ካወቀውም እግዚአብሔር ያወቀው ነገር ዋጋው ታላቅ ነው፡፡ የክርስትና እምነት እዩኝ እዩኝንና እወቁኝ እወቁኝ ማለትን አይፈልግም! ክርስቲያን ክርስቲያንነቱንና የክርስትና ሥራዎቹን ለሰዎች በልፈፋ ማስታወቁና ውዳሴ መቀበሉ ያዋርደዋል እንጂ አያከብረውም፡፡ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከምጽዋትና ሊደበቁ ከማይቻላቸው የጽድቅ ሥራዎች በስተጀርባ ራሱን፣ ማንነቱንና ሥራዎቹን የማይሸሽግ ክርስቲያን በክርስትና እምነት ውስጥ «ክርስቲያን» ከሚለው ስሙ በስተቀር ምንም ዓይነት ድርሻ ሊኖረው አይችልም፡፡


ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ የጽድቅ ሥራዎችን ሠርተው ራሳቸውን የሚሸሽጉ ታላላቅ አባቶች ለእርሷ አባቶቿም መመኪያዎቿም ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ብዙ ሠርተው ጥቂት እንኳ ያልተናገሩ ብዙ ልጆች አሉት፡፡ አበ ብዙኀን አብርሃም፣ ነቢዩ ሙሴ፣ ነቢዩ ዳዊት፣ መጥምቁ ዮሐንስና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተው ከእግዚአብሔር ዘንድ ልዩ ቦታ ያገኙ ሰዎች ቢሆኑም ለታይታ እና በዚህ ሳቢያ ለሚመጣው ሙገሳ፣ ውዳሴና ከበሬታ ራሳቸው ሊያሳዩ ያልፈለጉ ወይም ለመፈለግ ያልሞከሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በአንጻሩ ራሳቸውን በትሕትና እጅግ ዝቅ አድርገው ማንነታቸውን ከአፈር፣ ከአመድ፣ ከትል፣ ከጭንጋፍ ጋር ሲያስተካክሉ ሰምተናቸዋል፡፡


አንድ ሰው እንኳንስ ስለ ራሱ ድኅነት ለሚበጀው ነገር ቀርቶ ስለ ሌሎች ሰዎች ሲል በሚያደርገው የጽድቅ ሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብተው ሊያወድሱትና ሊያሞግሱት ቢሞክሩ እንኳ ሊመልስ የሚገባውን ነገር ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ በማለት አሳስቦታል፡- «እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፡- የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፤ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ» ሉቃ 17፥19፡፡ የጽድቅ ሥራዎችን ሠርተው ሰዎች እንዲያዩላቸው የሚፈልጉ ግብዝ ሰዎች በዚህ ቃል ፊት እንዴት ሊቆሙ እንደሚችሉ ሳስብ እጅግ እደነቃለሁ፡፡ ሠርቶ ሠርቼያለሁ ብሎ መገበዝና ሠርቶ ውዳሴ ሲቀርብለት የማልጠቅም ባሪያ ነኝ ብሎ መናገር እንዴት ነው በአንድ ሚዛን ላይ ተቀምጠው ሊመዘኑ የሚችሉት? ሰዎች ሥራዎቻቸውን እንዲያዩላቸው የሚፈልጉና ከአዩ በኋላ ውዳሴ የሚያቀርቡላቸው ሰዎች ዋጋቸውን የሚያገኙት ከእነዚሁ ሰዎች ሲሆን የሠሯቸውን ሥራዎች ሰዎች አይዩብን ብለው የሚሸሽጉት ሰዎች ደግሞ ዋጋቸውን የሚያገኙት ከእግዚአብሔር ነው፡፡ የሚበልጠውም ዋጋ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የጽድቅ ሥራ የሆነውን ጾም ወይም ጸሎት ወይም ምጽዋት በስውር የሚሠራ ከሆነ እግዚአብሔር አምላክ በሁለተኛ አመጣጡ በግልጽ ስለሚሰጠው ነው፡፡


በስውር ሠርቶ በግልጽ መቀበል ታላቅ ዋጋ ያስገኛል፤ እንዲህ ዓይነቱ ሥራ ከሙገሳ፣ ከውዳሴና ከከበሬታ የጸዳ ነውና፡፡ ይህ ስለሆነ ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ውስጥ እንዲህ በማለት የተናገረው፡- «መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ» ማቴ 5፥16፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን «ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ» የሚለውን የጌታ ቃል ነው፡፡ በሰዎች ፊት ሊሸሸጉ የማይችሉትን ወይም በሰዎች ፊት እንዲሁ ይብሩ የተባሉትን የጽድቅ ሥራዎች የሚመለከቱ ሰዎች እነዚህን የሰዎች የጽድቅ ሥራዎች ቢመለከቱ እንኳ ሰዎቹን እንዲያከብሩ ወይም እንዲያወድሱ ወይም እንዲያሞግሱ አልተፈቀደላቸውም፤ እነዚህን የጽድቅ ሥራዎች እንዲሠሩ የፈቀደላቸውን፣ ያነሣሣቸውን፣ ያስጀመራቸውንና ያስፈጸማቸውን አምላክ እንጂ፡፡ በአጠቃላይ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመን ሊደበቁ ከማይችሉት የጽድቅ ሥራዎች በስተቀር ጾምን፣ ጸሎትን፣ ምጽዋትን፣ ስግደትን፣ . . . ወዘተ በሰዎች ፊት እንዲሠራ ስላልተፈቀደለት የተፈቀዱለትን ሥራዎች ብቻ በመሥራት ጽድቅን ገንዘቡ እንዲያደርግ ይመከራል፡፡ የጽድቅ ሥራዎቹን በሰዎች ፊት አቅርቦ የሚያልፈውን የሚጠፋውን ከንቱ ከበሬታ፣ ከእነርሱ እጅ ከሚቀበልም በስውር ተመልክቶ በመጨረሻው ቀን ዘለዓለማዊ ዋጋውን ከሚከፍለው ከእግዚአብሔር እጅ እንዲቀበል ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፡፡


አንዳንድ ጊዜ በክርስትና እምነት ውስጥ የሰው ዕውቀት፣ ችሎታ፣ ልምድ፣ ደረጃ፣ ማዕርግ፣ ጥበብ፣ ስጦታ፣ ዘር፣ እና ሌሎች እነዚህን የሚመስሉ ነገሮች በሰዎች ዘንድ መገኘታቸውን ከመሰወር ይልቅ ይፋ አውጥቶ በእነዚህ ነገሮች ምድራዊ ዋጋ ለመቀበል መደራደር ተቀባይነት የለውም፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ይልቅ ሁሉም ነገር እያላቸው እንደ ሌላቸው የሚሆኑ፤ በእነዚህ ሀብቶቻቸው በምድር ላይ የሚገለገሉ ሰዎችም እንደማይገለገሉባቸው የሚያስቡ፤ በዚህች ዓለም የሚጠቀሙም እንደማይጠቀሙባት የሚሆኑ ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚቀበሉት ዋጋ እጅግ የላቀ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህች ዓለም መልክና ብቃት በሙሉ አላፊ ናቸውና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል «. . . የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፤ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና» 1ኛ ቆሮ 7፥30-31፡፡ ስለዚህ በምታልፍ ዓለም ውስጥ የሚያልፍ ዋጋን በሰዎች ፊት አቅርበን በምድር የሚያስቀር ዋጋችንን ከእነርሱ ከምንቀበል ይልቅ የማያልፈውንና የማይጠፋውን ዋጋ ዘለዓለማዊ ከሆነው ከእግዚአብሔር በመቀበል የማታልፍ መንግሥቱን ለመውረስ ያብቃን፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤አሜን፡፡


ይቆየን፡፡

በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment