Friday 24 February 2012

ኪዳነ ምሕረት


ኪዳነ ምሕረት


የካቲት 15/2004 ዓ.ም.
በገብረ እግዚአብሔር ኪደ
Kidane meherete
ኪዳን ማለት በሁለት ወይም ከሁለት በላይ በሆኑ ወገኖች መካከል የሚደረግ ስምምነት፣ ውል ማለት ነው፡፡ ውል “ውል” የሚያሰኘው በውሉ ወይም በስምምነቱ ውስጥ ያሉት ወገኖች እያንዳንዳቸው የሚጠበቅባቸውንና ሊያደርጉት የሚገባቸውን ተግባር ሲኖር ነው፡፡ የሚፈርሰው እንኳ ሁሉም ወገኖች ሲስማሙ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ወገን ብቻ ቢያፈርስ ግን እርሱ ውል አፍራሽ ይባላል፡፡ ሓላፊነቱንም እርሱ ይወስዳል፡፡



በምሥጢራዊ ትርጕሙ ግን ኪዳን ማለት እግዚአብሔር ስለ ፍቅሩ፣ ስለሚሰጣቸው ተስፋ፣ ስለ እነርሱ ረብሕና ጥቅም ከሰው ልጆች ጋር የሚያደርገው የይቅርታ፣ የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ይህም ኪዳነ ምሕረት ይባላል፡፡

አዎ! እግዚአብሔር ልጆቹ ይጠቀሙ ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቅዱሳኑ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ከእነዚህም ኪዳነ አዳም፣ ኪዳነ ኖኅ፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ዳዊት እንዲሁም በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በሙሉ የተሰጠ ሐዲስ ኪዳን ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እግዚአብሔርን በፍጹም ኀይላቸው፣ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ለወደዱትና ላገለገሉት ወዳጆቹ ስለሚሰጣቸው ቃል ኪዳን በነብዩ አንደበት እንዲህ ብሏል፡- “ሰንበቴን ቢጠብቁ ደስ የሚያሰሰኘኝንም ነገር ቢመርጡ በቃል ኪዳኔም ጸንተው ቢኖሩ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምንም እሰጣቸዋለሁ” /ኢሳ.56፡4-5/፡፡ ለዚህም ነው የቅዱሳንን ገድል ስናነብ “ስምህን ለሚጠራ፣ በስምህ ለሚማፀን፣ መታሰብያህን ለሚያደርግ፣ ገድልህን ለሚጽፍና ለሚያጽፍ፣ ለሚያነብና ለሚሰማ እንዲህ እንዲህ አደርግለታለሁ” በሚል ቃል ኪዳን ተጠናቅቆ የምናገኘው፡፡ አለፍ ሲልም ለአንዳንድ ቅዱሳን “እስከ አሥርና ሠላሳ ትውልድ ድረስ ከዚያም በላይ እምርልሃለሁ” የሚል ቃል ኪዳን ተሰጥተዋቸው እናያለን፡፡

ሆኖም ግን እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ለቅዱሳን ይህን የመሰለ ቃል ኪዳን ቢሰጣቸውም የዚያ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ መሆን የምንችለው አስቀድመን በአሚነ ሥላሴና በምግባር ስንገኝ ብቻ ነው፡፡ አዎ! የእነዚህ ቅዱሳን ልጆች መሆን የምንችለው ደግሞም የእነርሱን ቃል ኪዳን ተጠቃሚ የምንሆነው እነርሱ በኖሩበትና አምላካቸውን ደስ ባሰኙበት የሕይወት መስመር ስንሰማራና ስንጓዝ ብቻ ነው /ማቴ.3፡9 ፣ዮሐ.8፡39-41/፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን “በላዔ ሰብእ” ብለን የምንተርከው የእመቤታችን ፍቅር የሚጸናበት ስምዖን የሚባል ሰው አለ፡፡ ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን፡- ስምዖን አስቀድሞ ፍጹም እንግዳ ተቀባይና አብርሃምን የመሰለ ደግ ሰው ነበረ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ “የወንድማማች መዋደድ ይኑር። እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና” ያለውን ቃል ለመተግበር የሚተጋ ሰው ነበረ /ዕብ.13፥1-2/፡፡ ታድያ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ በስምዖን ይቀናና ልክ በአብርሃም ቤት ሥላሴ እንደተስተናገዱ ራሱን የብርሃን መልአክ በመምሰል በሦስት ሰው አምሳል ወደ ቤቱ ሔደ፡፡ ስምዖንም አብርሃም እንዳደረገው እግራቸውን አጥቦ የሚበላ ነገር ሰጣቸው፡፡ በመጨረሻም “ልጅህን ሠዋልን” ብለውት ሠውቶላቸዋል፡፡ የልጁን ሥጋ ሲያቀምሱትም ሰይጣን ወደ ልቡ ገባ፡፡ በላዔ ሰብእም ሆነ፡፡ ቤተ ሰዎቹንም በልቶ ጨረሰ፡፡ እንዲህ እያደረገም 78 ሰው በላ፡፡ የስም ክርስቲያን ሆኖ ቀረ፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ስምዖን ያደረገውን ሁሉ ያደረገው እርሱ ራሱ ክፉ ሆኖ ሳይሆን ባለማወቅ እንዳደረገው  ስለሚያውቅ (ለምሳሌ ደግነቱ እንዳለ ሆኖ ልጅ መሠዋት ግን በሐዲስ ኪዳን እንደማይደረግ አያውቅም!) እግዚአብሔር ከግብሩ እንዲመለስ ሁኔታዎችን አመቻቸለት፡፡ ጊዜ ለኵሉ እንዲል፡፡ አንድ በጣም ደሀና በበሽታ የተቆራመደ ሰውም መንገድ ላይ አስቀመጠለት፡፡ ስምዖን ያንን ደሀ ቢያየውም እንዳይበላው ተጸይፎት አለፈ፡፡ ድሀው ግን “ስለ ድንግል ማርያም እባክህን ውኃ አጠጣኝ?” ሲለው “ይህን ስም አውቀዋለሁ፤ መጽናኛዬም ነበር” ብሎ ወደ ልቡ ተመለሰና (ከድሮ ግብሩ ተጸጸተና)፡- “ማንም ከታናናሾቹ በደቀ መዝሙሬ ስም ቀዝቃዛ ውኃ ቢያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም” የሚለው የወንጌል ቃል ድሮም እርሱ ራሱ ሲያደርገው የነበረውን ነገር ትዝ ይለዋል /ማቴ.10፡42/፡፡ ትዝ ብሎትም አልቀረ ልቡ ራርቶ ለዚያ ደሀ ውኃ አጠጣው፡፡ አስቀድሞ በአሚነ ሥላሴ ነበረና ለመመለስም ፍቃደኝነቱን አሳይቷልና በእመ አምላክ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ ሆነ (ድርሳን ዘኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 የሚነበብ)፡፡

ከዚህ እንደምንረዳው አንድ ሰው የቅዱሳንን ቃል ኪዳን ለመጠቀም አስቀድሞ በአሚነ ሥላሴ መኖር፤ በንስሐ መመለስ፣ ኪዳነ ቅዱሳንን የሚያምንና ፍቅራቸው ያደረበት፣ መልካም ምግባር ለማድረግም የሚጣጣር መሆን እንዳለበት ነው፡፡ አለበለዚያ ግን የቅዱሳን ቃል ኪዳን እርሱን ወክሎ ሃይማኖትና ምግባር ሊሆነው አይችልም፡፡ እስራኤላውያን ምንም እንኳን ከአብርሃም በሥጋ ቢወለዱም የአብርሃምን ምግባርና ሃይማኖት ይዘው ስላልተገኙ እግዚአብሔር ለአብርሃም፡- “በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ” ብሎ በማለለት ቃል ኪዳን መጠቀም አልቻሉም /ገላ.3፡6-9/፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የገባላቸውን ውል እነርሱ ራሳቸው አፍርሰውታልና፡፡ እግዚአብሔርን ክደውታልና፤ ለበአል ሰግደዋልና፤ ነብያትን ገድለዋልና፤ ጌታን ሰቅለዋልና፤ ሐዋርያትን አሳድደዋልና፡፡ በእርግጥም በክሕደትና በኀጢአት የምትዳክር ነፍስ የንስሐ ፍሬ ለማፍራትና ለመመለስ የማትጣጣር ከሆነ  በቅዱሳን ቃል ኪዳንና ምልጃ እንዲሁ መዳን አትችልም /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ Homily on the Gospel of St. Matthew, Hom.5/፡፡

አስቀድመን እንዳልነው በላዔ ሰብእ የተጠቀመው በእመአምላክ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጇ የሚላቸውን ለሚፈጽሙ፤ ወላዲተ አምላክነቷን ለሚመሰክሩ፤ አማላጅነቷን አምነው ለሚማጸኑ ሁሉ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የሰጣት የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷታልና፡፡ ልጇ ወዳጇ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በመምጣት፡- “እናቴ ሆይ! ከእኔ የምትፈልጊውን ለምኚ፤ እኔም የለመንሽኝን ሁሉ እፈጽምልሻለሁ” ሲላት፡- “ልጄ ወዳጄ! ስለ እኔ የታረዘውን ያለበሰ በሰው እጅ ያልተሠራ ዕፁብ ድንቅ የሆነውን፣ የማይጠፋውን፣ የማያረጀውን፣ እውነተኛውን ልብስ አልብስልኝ፤ አቤቱ! ስለ እኔ ስም በሽተኞችን የጠየቀ በቸርነትህና በይቅርታህ ጐብኝልኝ፤ አቤቱ! ስለ ስሜም ብሎ ለተራበ ያበላውን አንተ የሕይወት እንጀራ አብላው ሰማያዊ በሆነ ማዕድህም አስቀምጥልኝ…” ስትለው ጌታችንም “እንዳልሽ ይሁንልሽ” በማለት ይህንና ሌላ ብዙ ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ እመቤታችንም ስለ ገባላት ቃል ኪዳን በፍጹም ደስታ አምላኳን አመስግናለች፡፡ ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል ይህን ቢገባው በአንክሮ፡- “በከመ ይቤ መጽሐፍ ማእከለ ፈጣሪ ወፍጡራን ለዕረፍት ዘኮንንኪ ጽላተ ኪዳን- መጽሐፍ እንዳለ በፈጣሪና በፍጡራን መካከል የዕረፍት መንግሥተ ሰማያት ውል፣ ስምምነት የተጻፈብሽ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ጽላት ነሽ” ይላታል፡፡

ይህም የሆነው የካቲት አሥራ ስድስት ስለ ነበረ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ የዚሁ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ ሆነው ይገኙ ዘንድ እያስተማረች በየዓመቱ ይህን ቀን በደመቀ ሁኔታ ታከብረዋለች፡፡

እንደ በላዔ ሰብእ እርሱ ያዘጋጀልን የንስሐን ደወል እንድንሰማ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡ እመ አምላክም በቃል ኪደኗ ትራዳን አሜን ለይኩን ለይኩን!!!

No comments:

Post a Comment