Tuesday 21 February 2012

የዐቢይ ጾም ስብከት (ክፍል 1) በአያሌው ዘኢየሱስ


የዐቢይ ጾም ስብከት (ክፍል 1)



የካቲት 13/2004 ዓ.ም
በአያሌው ዘኢየሱስ

ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት በሆነችው በቅድስቲቱ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ጾም እንደ እንግዳ ደራሽ፤እንደ ወንዝም ፈሳሽ በድንገት የተጀመረ ሥርዓተ አይደለም፡፡ በተለይም በአዲስ ኪዳን ዘመን ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን መድኀኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የመጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡



 ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ በአንድ ወቅት ከመጥምቁ ዮሐንስና ደቀ መዛሙርት ጾምን አስመልክቶ የቀረበለት ጥያቄና የሰጠው መልስ አለ፡፡ ያቀረቡለት ጥያቄ፡- «. . .  እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው፤ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ለምንድር ነው?» (ማቴ 9፡14)  የሚል ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡- «. . . ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን; ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤በዚያን ጊዜም ይጦማሉ፡፡» ማቴ 9፡15፡፡ ጌታ በዚህ መልሱ ውስጥ ራሱን  በሙሽራ ደቀ መዛሙርቱንም በሚዜዎች በመመሰል እርሱ በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ ከእነርሱ በዕርገቱ ተለይቶ ከመሔዱ በፊት ሊያዝኑ፣ ሊተክዙና ከመባልዕት ሊከለከሉ እንደማይችሉ ነገር ግን በዕርገቱ ሲለያቸው መጾም እንደሚጀምሩ ተናገረ፤አስተማረ፡፡ በመሆኑም «በዚያን ጊዜም ይጦማሉ፡፡» የሚለው ሐረግ እርሱ በገዳመ ቆሮንቶስ የጣለውን የጾም መሠረት እነርሱ ከዕርገቱ በኋላ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት የሚያጎላ ነው፡፡

ሃይማኖትንና የአምልኮ ሥርዓቶችን ከሐዋርያት አባቶቿ የተማረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ለምእመናን ልጆቿ የጾም ሥርዓቶች ደንግጋ ሥጋቸውን በማድከም ለመንፈሳዊ ሥራ እንዲተጉ ማድረግ ከጀመረች ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የፈቃድ ጾም የሆነችውን የጽጌ ጾም እንዲሁም የግል ጾምን ሳይጨምር ሰባት ዋና ዋና አጽማዋት አሉ፤እነርሱም እንደ ቅደም ተከተላቸው፡- የድኅነት ጾም (ረቡዕና ዓርብ)፣ የነቢያት ጾም (የገና ጾም)፣ የገሃድ ጾም፣ የነነዌ ጾም፣ ዐቢይ ጾም፣ የሐዋርያት ጾም (የሰኔ ጾም) እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው የሚጾሙበት የራሳቸው የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ያላቸው ሲሆን ለጊዜው ግን የመጀመሪያውንና ዋናውን ጾም ይኸውም ዐቢይ ጾምን እንመለከለታለን፡፡

ይህ ጾም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ በገዳመ ቆሮንቶስ ለአርባ ቀናት የጾመው ጾም ነው፡፡ ምሳሌው፣ አብነቱና አርአያነቱ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤የማቴዎስ ወንጌል «አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ጦሞ በኋላ ተራበ፡፡» (ማቴ 4፡2) ይላልና፡፡ በዚህ ጦሙም ሰይጣን ወደ እርሱ ቀርቦ በሦስት ዋና ዋና ኀጢአቶች (አርእስተ ኀጣውእ) ፈትኖታል፡፡ ገና ከመጀመሪያው ለምን ይጾም ዘንድ ወደ ገዳም ለመሔድ ወደደ? ለምንስ ጾመ? ለምንስ በሰይጣን ተፈተነ? ብለን ስንጠይቅ ዲያብሎስ በእርሱ ላይ የሚያረቀው በደልና ኀጢያት ኖሮበት ሳይሆን እኛን ተጠመቁ ሊለን እንደተጠመቀ እርሱ ጾሞ እኛን ጹሙ ሊለን ጾመ የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ እኛ በምንጾምበት ጊዜ ሰይጣን እንድንበላ፣ ጌታን እንድንፈታተንና ለሀብትና ለንብረት እንድንበረከክ ሊያደርገን እንደሚመጣና ያን ጊዜም በእግዚአብሔር ቃል ድል ልናደርገው እንምንችል ሊያስተምረን ሲል እርሱ ጾመ፡፡ በተለይም ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ጭምር እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊገልጥልን ይህን አደረገ፡፡

ዐቢይ ጾም የሚጾመው ለስምንት ሳምንታት ወይም ለአምሳ ስድስት ቀናት ያህል ነው፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል? ጌታ የጾመው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት አይደለም ወይ? ብንል በእነዚህ 56 ቀናት ውስጥ   የሚገኙትን 7 ቅዳሜዎችና 8 እሑዶች ስንደምራቸው አሥራ አምስት ቀናት ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ከጥሉላት እንከልከልባቸው እንጂ ከእህል ውኃ ስለማንከለከልባቸው እነዚህ 15 ቀናት ከዋናዎቹ የጾም ቀናት ገብተው አይቆጠሩም፡፡ ይህ ደግሞ ትክክለኛውን የጾም ቁጥር ወደ አርባ ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ጾሙ «ዐቢይ» የተባለውም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ ስለሆነ እና ታላላቅ የተባሉት ሦስት ኀጢአቶች ማለትም ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ነዋይ ድል የተነሡበት ጾም ስለሆነ ነው፡፡

በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙት 8 እሑዶች እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ስያሜ አላቸው፡፡ የሰንበታቱ ስያሜ መሠረት የሆነው በዐቢይ ጾም ሊዘመር የተዘጋጀው የጾመ ድጓው መዝሙር ነው፡፡ በየሰንበቱ የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት (ወንጌል፣ መልእክታትና የሐዋርያት ሥራ)፣ የሚዘመረው የዳዊት መዝሙር (ምስባክ) ከሰንበቱ ስያሜ ጋር የሚያያዙና የሚዛመዱ ናቸው፡፡ በሰንበታቱ ውስጥ የሚነበበውና የሚዘመረውም ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ያስተማራቸውን ትምህርቶችና የሠራቸውን ዋና ዋና ተአምራትና መንክራት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ጾሙ የጌታ ጾም ስለሆነ ሁሉም መዝሙራትና ምንባባት ከጌታ ትምህርትና ሥራ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የስምንቱ እሑዶቹ ስያሜዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው የሚከተሉት ናቸው፡- ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መፃጒዕ፣ ደብረ ዘይት፣ ገብር ሔር፣ ኒቆዲሞስ እና ሆሳዕና፡፡

በመቀጠል በስምንቱ እሑዶች ውስጥ የሚነበቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባትና የሚቀርበው ምስባክ በጽሑፍ ካቀረብን በኋላ የሚሰበከውንም የወንጌል ስብከት በጽሑፍ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

አነሣሥቶ የሚያስጀምርና አስጀምሮ የሚያስፈጽም እግዚአብሔር ለቅዱሳን አባቶቻችን የገለጠውን ምሥጢር ለእኛ ለባሪያዎቹ እንዲገልጥልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤አሜን፡፡

† የመጀመሪያው የዐቢይ ጾም ሰንበት (ሳምንት) ስያሜ፡-
ዘወረደ፡፡
† የሰንበቱ የወንጌል ንባብ፡-
ዮሐ 3፡10-25፡፡
† የንባቡ ዋና ርእሰ ጉዳይ፡-
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ሥጋ ለብሶ ለማዳን መውረዱንና መወለዱን የሚናገር ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡
† የዕለቱ ምስባክ፡-
“አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ፤እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ፡፡ ለእግዚአብሔር በፍርሀት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ፡፡” መዝ 2፡11
† ከዚህ የወንጌል ንባብ ለዛሬ የተወሰደው ኀይለ ቃል፡-
«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡» ዮሐ 3፡16፡፡ 
† ተዛማጅ (አጎላማሽ) ጥቅሶች፡-
ዕብ 13፡7-17፣ ያዕ 4፡6፣ ሐዋ 25፡13-ፍጻሜ፡፡

† ስብከተ ወንጌል፡-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የሰው ልጆች በኀጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔርን የሚያህል ጌታ እና ገነትን የምታህል ቦታ ካጡ በኋላ ቸርነት፣ ደግነትና ርኅራኄ ልዩ የባሕርይ ገንዘቦቹ የሆኑት መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ያጡትን ጌታ እና ቦታ መልሶ ይሰጣቸው ዘንድ ከ5500 ዓመታት በኋላ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ለብሶ ተወልዶ፣ ተጠምቆ፣ አድጎ፣ ጾሞ፣ ጸልዮ፣ ተአምራት ሠርቶ፣ አስተምሮ፣ ፈውሶ፣ ተከሶ፣ ተንገላቶ፣ መከራ ተቀብሎ፣ ሞቶ፣ ከሙታን መካከል ሞቱን በሞቱ ሽሮ፣ ተከታዮቹን አጽንቶና ወደ ቀደመ ክብሩ በመመለስ አድኗቸዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ወርዶ እነዚህን ሁሉ ሥራዎች የሠራው ነቢያት አስቀድመው «ፈኑ እዴከ እም አርያም፤. . .» «እጅህን ከሰማይ ላክና አድነን፤» እያሉ ወደ መንበረ ጸባዖት ይጮሁ ስለ ነበር ነው፡፡ እርሱም ይህ ጩኸታቸውና በፍዳ መኖራቸው ስላሳዘነው ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ እና ከባሕርይ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር መተካከልን ከመቀማት ሳይቆጥር ያድነን ዘንድ ወደ ምድር ወረደ፤ወርዶም ሥጋን በመልበስ አዳነን፡፡ ስለሆነም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሱ እንዲህ በማለት ተናገረ፡- «እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፤ነገር ግን የባርያውን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፤ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ፡፡» ፊልጵ 2፡6-8፡፡

በእኛ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ እኛ ስለ ሌሎች ሰዎች ክብር ስንል ራሳችንን ዝቅ ከማድረግና ከማዋረድ ይልቅ ከፍ ማድረግና ማክበር ነው የሚቀናን፡፡ ከመታዘዝም ይልቅ ማዘዝ ልዩ መታወቂያችን ነው፡፡ ክብርንና ከሌሎች ሰዎች ጋር መተካከልን ከምናጣ ይልቅም ዕለቱን ሞታችንን የምንመርጥ ሰዎች ብዙዎች ነን፡፡ ዛሬ ክብርን አለመሻት፣ ራስን ማዋረድና ለሌሎች መታዘዝ ቁልፍ የክርስትና መርሖዎች መሆናቸው የሚያውቁ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ እኛን ለክብር የሚያበቃን ስለ ሌሎች ሰዎች ስንል የራሳችንን መደላደል ማጣታችን ነው፡፡ የክርስትና እምነት የተመሠረተችው እያጡ በማግኘት፣ እየተራቡ በመጥገብ፣ ሳይታወቁ በመታወቅ፣ ኀዘንተኛ ሆኖ በመደሰት፣ ድሀ ሆኖ ብዙዎችን ባለ ጠጎች በማድረግ፣ እየቀነሱ በመደመር፣ እያካፈሉ በማብዛት፣ እየተሰደዱ መንግሥተ ሰማያትን በመውረስ ላይ ነው፡፡ ለዘመናችን ሰው ያለህን ሁሉ እጣውና ታገኘዋለህ፤ተርበህ ትጠግባለህ፤ድሀ ሆነህ ሌሎችን ባለ ጠጎች ታደርጋለህ፤ተዋርደህም ከፍ ትላለህ ቢባል ፍጹም ሊገባው አይችልም፡፡ ብዙዎቻችን አምላካችን እግዚአብሔርን እኛን ባለ ጠጎች ለማድረግ እርሱ ድሀ እንደ ሆነ ብናስተውል እኛም ስለ ሌሎች ድኆች በመሆን እነርሱን ማዳን እንችል ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ የተናገረው ቃል ምንኛ ድንቅ ነው፡- «. . . እናንተ በእርሱ ድግነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ፡፡» 2ኛ ቆሮ 8፡9፡፡

ከላይ ለወንጌል ስብከታችን ርእስ አድርገን የተነሣንበት ቃል የሚያስተምረንም ይህንኑ ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ነው ሁላችን በእርሱ አምነን የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ እንጂ እንዳንጠፋ ሲል ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን አንድ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን ለእኛ እስኪሰጥ ድረስ እንዲሁ የወደደን፡፡ እርሱ አንድያ ልጁን ለእኛ መሥዋዕት እንዲሆን የሰጠን እኛ እንድንድን ነው፡፡ በሁዳዴ ወይም በዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ ልናስበው የሚገባን ዐቢይ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ «ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡» የሚሉት ቃላት ምንኛ ጥልቅ ናቸው! እግዚአብሔር ከሰማየ ሰማያት እንዲወርድ ያደረገው ዓለሙን እንዲሁ ስለ ወደደው ነው፡፡ እርሱ ወደ እኛ የወረደው እኛ ስለ ወደድነው አይደለም፤እርሱ ስለ ወደደን እንጂ፡፡ እኛ ልባችንንና ዐይኖቻችንን ወደ እርሱ ከፍ ማድረግ አቅቶን በጨለማ ውስጥ ስንዳክር ነው እርሱ ከዚህ ጨለማ ውስጥ ያወጣን ዘንድ ክብሩን ትቶ ወደ እኛ የወረደው፡፡

የግብጽ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ቅዱስነታቸው አቡነ ሲኖዳ ይህን አስመልክተው በአንድ መንፈሳዊ መጽሐፋቸው ውስጥ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፡- «When we were not able to ascend to him he descended to us./ እኛ ወደ እርሱ መውጣት ሲያቅተን እርሱ ወደ እኛ ወረደ፡፡» እንደ ማለት ነው፡፡ በእርግጥም የኀጢአቶቻችን ብዛት እኛን ከእርሱ እጅግ የሚያርቁ ቢሆኑም እርሱ ይህን ርቀታችንን ለማጥፋት ሲል ነው ወደ እኛ የወረደው፡፡ እርሱ እኛን እንዲሁ (ያለ ምንም በጎ ሥራ) ስለ ወደደን ነው አንድያ ልጁን የሰጠን፡፡ እንዲሁ ማለት ምንም ሳይኖረን ማለት ነው፡፡ እንዲሁ ማለት ከእኛ ምንም ሳይፈልግ ማለት ነው፡፡ እንዲሁ ማለት ከእኛ የሚከፈል ምንም ዋጋ ሳይፈልግ ማለት ነው፡፡ እንዲሁ ወዶአል ማለት የሚያስወድድ ሥራ ባይኖረንም እንዲሁ በችሮታው በጸጋው ወዶናል ማለት ነው፡፡ እርሱ ዓለሙን ወይም እኛን እንዲሁ ወዶአል ማለት መወደድ ባይገባንም እንዲሁ ወዶናል ማለት ነው፡፡

የወደደን እኛ ሳንወደው ነው፡፡ እኛ ሳንወደው ነው እርሱ አስቀድሞ የወደደን፡፡ ይህ ስለሆነ ነው ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ «ፍቅርም እንደዚህ ነው፤እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኀጢአታችን ማስተሰሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም፡፡» (1ኛ ዮሐ 4፡10) በማለት የጻፈልን፡፡ እርሱ እንዲሁ የወደደን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነን የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ እንጂ እርሱን ከክብሩ በማሳነስ ወይም የለህም በማለት በክህደት እንዳንጠፋ ነው፡፡ እርሱ እኛን የወደደን እርሱ የወደዳቸው ጻድቃኑንና ቅዱሳኑን እንድንወድለት ነው እንጂ በድፍረት፣ በትዕቢትና በመናቅ በእነርሱ ላይ ክፉ እንዳንናገር ነው፤እንዲህ ያሉ የሽንግላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ ተብለው ተረግመዋልና፤መዝ 30፡18፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለእኛ የሰጠን ፊተኛዋና ታላቂቱ ትእዛዝ «ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ፡፡ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት፡፡» (ማቴ 22፡37-38) የምትለዋ ናት፡፡ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረን ስለሚወደን ነው፡፡ እርሱ ይህን ፊተኛና ታላቅ ትእዛዝ የሰጠን እርሱ እንደ ወደደን እኛም እርሱን እንድንወደው ነው፡፡ ትእዛዙ ፊተኛና ታላቅ እንደ መሆኑ ማንንም ከመውደዳችን በፊት እግዚአብሔርን መውደድ ይገባናል፡፡ በእኛ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር አስቀድመን የምንወዳቸው ብዙ ነገሮች አሉን፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሆዱን የሚወድ ሰው አለ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ እንቅልፉን የሚወድ ሰው አለ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ገንዘቡን የሚወድ ሰው አለ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ንብረቱን የሚወድ ሰው አለ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ዘመዶቹን፣ ወገኖቹን፣ ቤቱንና አገሩን የሚወድ ሰው አለ፡፡

ይህ ሁሉ ግን ከንቱ ነው፤ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊበልጥ አይችልምና፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከእግዚአብሔር ይልቅ ሆዱንና እንቅልፉን ስለሚወድ ጠዋት ለጸሎት ቀን ለቅዳሴ ሲተጋ አይታይም፡፡ ገንዘቡንና ንብረቱን ከእግዚአብሔር አስበልጦ ስለሚወድም በሚወደው ገንዘቡና በንብረቱ ማንኛውንም ነገር ማድረግ እችላለሁ ብሎ ስለሚመካ በእግዚአብሔር መመካት እንደሚገባው ቢነገረው ሊሰማ አይችልም፡፡ ቤቱንና ቤተሰቦቹን እንዲሁም ወገን ዘመዶቹን በተመለከተም ከጌታ ይልቅ እነርሱን አስበልጦ የሚወድ ከሆነ ለእርሱ የሚገባ አለመሆኑ እንዲህ በማለት ገልጾአል፡- «ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ከእኔም ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤. . .» ማቴ 10፡37፡፡

ሰው ለእግዚአብሔር ካልሆነ ለማነው ሊሆን የሚችለው? እግዚአብሔር አምላክ ለእኔ ሊሆን አይገባውም ያለው ሰው መግቢያስ ወዴት ሊሆን ነው? እርሱን አስበልጦ ከመውደድ ይልቅ ሌሎችን የሚወድ ሰውስ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው? ይህ ከመሆኑ በፊት ግን እርሱን ለመውደድ ልባችንን፣ ነፍሳችንንና ዐሳባችንን ፍጹም ለማድረግ ልናስለምድ ይገባናል፡፡ ዛሬ የእግዚእሔርን ትእዛዛት መጠበቅ እያቃተን ዘወትር በኀጢአት የምንሰነካክለው እርሱን መውደድ ስላልቻልን ነው፤እርሱ «ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠበቁ፡፡» (ዮሐ 14፡15) በማለት ተናግሯልና፡፡ ሕግ በመተላለፍ የምንሰርቀው፣ የምንዋሸው፣ በሐሰት የምንመሰክረው፣ የምንገድለው፣ ክፉ የምንመኘውና ሌሎቹንም ኃጢአቶች የምንፈጽመው እግዚአብሔርን ስለማንወደው ነው፡፡ ይህን የምንፈጽም ሆነን እግዚአብሔርን እንወደዋለን የምንል ከሆንን መውደዳችን የአንደበት ብቻ እንጂ የልብ እንዳልሆነ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

ስለዚህ እኛን ለማዳን ሲል እኛን እንዲሁ የወደደንን እግዚአብሔር እንውደደው፡፡ በዚህ የመጀመሪያ የዐቢይ ጾም ሳምንት ውስጥ ጾሙን እርሱን በመውደድ ለመጀመር፤ጀምረንም ለመጨረስ እንዲያበቃን የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤አሜን፡፡

ይቆየን፡፡

በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment