የዐብይ ጾም ስብከት (ክፍል 2) |
የካቲት 15/2004 ዓ.ም. በአያሌው ዘኢየሱስ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤አሜን፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጾም በድንገት የተገኘ የሰዎች ፍልስፍና ሳይሆን አምላካዊ ሥርዓት ነው፡፡ ጾም መጾም የተጀመረበት ጊዜ ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጋር የማይተናነስ መሆኑን የምናውቀው እግዚአብሔር አምላክ የቀደሙ ወላጆቻችንን፡- ከዚህ ብሉ፤ ከዚህ ግን አትብሉ (ዘፍ 2፥16-17) በማለት ከደነገገላቸው ትእዛዝ ጋር የሚዛመድ በመሆኑ ነው፡፡ «አትብሉ» ማለት ከተወሰነ ወይም ከተወሰኑ መባልእት «ተከልከሉ» አልፎ ተርፎም «አትንኩት» ማለት ነው፡፡ ዲያብሎስ እናታችን ሔዋንን «በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዟአልን?» (ዘፍ 3፥1) በማለት በጠየቃት ጊዜ እግዚአብሔር ለእርሷና ለባሏ የሰጣቸውን ቀጥተኛ ትእዛዝ ግልጽ በሆነ መንገድ የነገረችው እንዲህ በማለት ነበር፡- «እግዚአብሔር አለ፡- እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፤አትንኩትም፡፡» ዘፍ 3፥3፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የአዳምንና የሔዋንን ሕልውና ወይም መኖርና አለመኖርን የወሰነው በመብላትና ባለመብላት ውስጥ ነበር፡፡ አዳምና ሔዋን መብላትን ችለው አለመብላትን ስላልቻሉ ነው ከገነት ተባርረው የሞት ሞት የተፈረደባቸው፡፡ |